ራእይ 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ራእይ 8:1-13

ሰባተኛው ማኅተምና የወርቁ ጥና

1በጉ ሰባተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ግማሽ ሰዓት ያህል በሰማይ ዝምታ ሆነ።

2ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባት መለከትም ተሰጣቸው።

3ሌላም መልአክ የወርቅ ጥና ይዞ መጣና በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ እርሱም በዙፋኑ ፊት ባለው የወርቅ መሠዊያ ላይ ከቅዱሳን ጸሎት ሁሉ ጋር እንዲያቀርበው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። 4የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳኑ ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ። 5መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበትና ወደ ምድር ወረወረው፤ ነጐድጓድ፣ ድምፅ፣ መብረቅና የምድር መናወጥ ሆነ።

ሰባቱ መለከቶች

6ከዚያም ሰባቱን መለከት የያዙት ሰባቱ መላእክት ለመንፋት ተዘጋጁ።

7የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ወደ ምድር ተጣለ፤ የምድር አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የዛፎችም አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የለመለመውም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።

8ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገር በእሳት እየተቀጣጠለ ወደ ባሕር ተጣለ፤ የባሕሩ አንድ ሦስተኛ ወደ ደም ተለወጠ፤ 9በባሕሩም ውስጥ ከሚኖሩት ሕያዋን ፍጡራን አንድ ሦስተኛ ሞተ፤ የመርከቦችም አንድ ሦስተኛ ወደመ።

10ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦ የሚነድድ ታላቅ ኮከብ በወንዞች አንድ ሦስተኛና በውሃ ምንጮች ላይ ከሰማይ ወደቀ፤ 11የኮከቡም ስም “እሬቶ8፥11 ምሬት ማለት ነው።” ይባል ነበር። የውሃውም አንድ ሦስተኛ መራራ ሆነ፤ ውሃው መራራ ከመሆኑ የተነሣም ብዙ ሰዎች ሞቱ።

12አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የብርሃናቸው አንድ ሦስተኛ ይጨልም ዘንድ፣ የፀሓይ አንድ ሦስተኛ፣ የጨረቃም አንድ ሦስተኛ፣ የከዋክብትም አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ የቀንም አንድ ሦስተኛ፣ የሌሊቱም አንድ ሦስተኛ ብርሃን እንዳይሰጥ ተከለከለ።

13ከዚያም ተመለከትሁ፤ አንድ ንስር በሰማይ መካከል ይበርር ነበር፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚነፉ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።