ሆሴዕ 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሆሴዕ 8:1-14

እስራኤል ዐውሎ ነፋስን ታጭዳለች

1“መለከትን በአፍህ ላይ አድርግ!

ሕዝቡ ቃል ኪዳኔን አፍርሰዋልና፣

በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና፣

ንስር በእግዚአብሔር ቤት ላይ ነው፤

2እስራኤልም፣ ‘አምላካችን ሆይ፤ እኛ እናውቅሃለን’ እያሉ፣

ወደ እኔ ይጮኻሉ።

3ነገር ግን እስራኤል በጎ የሆነውን ነገር ናቁ፤

ጠላትም ያሳድዳቸዋል።

4ያለ እኔ ፈቃድ ነገሥታትን አነገሡ፤

እኔንም ሳይጠይቁ አለቆችን መረጡ፤

በብራቸውና በወርቃቸው፣

ለገዛ ጥፋታቸው፣

ጣዖታትን ለራሳቸው ሠሩ።

5ሰማርያ ሆይ፤ የጥጃ ጣዖትሽን ጣዪ፤

ቍጣዬ በእነርሱ ላይ ነድዷል፤

የማይነጹት እስከ መቼ ነው?

6ይህም በእስራኤል ሆነ!

ባለ እጅ የሠራው ይህ ጥጃ፣ አምላክ

አይደለም፤

ያ የሰማርያ ጥጃ፣

ተሰባብሮ ይደቅቃል።

7“ነፋስን ይዘራሉ፤

ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ፤

አገዳው ዛላ የለውም፤

ዱቄትም አይገኝበትም፤

እህል አፍርቶ ቢገኝም፣

ባዕዳን ይበሉታል።

8እስራኤል ተውጠዋል፤

በአሕዛብም መካከል፣

ዋጋ እንደሌለው ዕቃ ሆነዋል።

9ለብቻው እንደሚባዝን የዱር አህያ፣

ወደ አሦር ሄደዋልና፤

ኤፍሬም በእጅ መንሻ ወዳጅ አበጀ።

10በአሕዛብ መካከል ራሳቸውን ቢሸጡም፣

እኔ አሁን እሰበስባቸዋለሁ፤

በኀያል ንጉሥ ጭቈና ሥር፣

እየመነመኑ ይሄዳሉ።

11“ኤፍሬም ለኀጢአት ማስተስረያ ብዙ መሠዊያዎችን ቢሠራም፣

እነርሱ የኀጢአት መሥሪያ መሠዊያዎች ሆነውበታል።

12በሕጌ ውስጥ ያለውን ብዙውን ነገር ጻፍሁላቸው፤

እነርሱ ግን እንደ እንግዳ ነገር ቈጠሩት።

13ለእኔ የሚገባውን መሥዋዕት ያቀርባሉ፤

ሥጋውንም ይበላሉ፤

እግዚአብሔር ግን በእነርሱ አልተደሰተም፤

ስለዚህ ክፋታቸውን ያስታውሳል፤

ኀጢአታቸውን ይቀጣል፤

ወደ ግብፅም ይመለሳሉ።

14እስራኤል ፈጣሪውን ረሳ፤

ቤተ መንግሥቶችንም ሠራ፤

ይሁዳም የተመሸጉ ከተሞችን አበዛ፤

እኔ ግን በከተሞቻቸው ላይ እሳትን እለቃለሁ፤

ምሽጎቻቸውንም ይበላል።”