1 ጴጥሮስ 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ጴጥሮስ 3:1-22

በባልና በሚስት መካከል ሊኖር የሚገባ ግንኙነት

1ሚስቶች ሆይ፤ እናንተም እንደዚሁ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ አንዳንድ ለቃሉ የማይታዘዙ ቢኖሩ፣ ያለ ቃል በሚስቶቻቸው አኗኗር ተማርከው ይመለሳሉ፤ 2ይህም የሚሆነው ንጹሕና ፍጹም አክብሮት የተሞላውን ኑሯችሁን ሲመለከቱ ነው። 3ውበታችሁ በውጫዊ ነገሮች በመሽሞንሞን፣ ይኸውም፣ ሹሩባ በመሠራት፣ በወርቅ በማጌጥና በልብስ አይሁን፤ 4ነገር ግን ውበታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ፣ ገርና ጭምት መንፈስ ያለበት፣ ምንጊዜም የማይጠፋ የውስጥ ሰውነት ውበት ይሁን፤ 5ተስፋቸውን በእግዚአብሔር ላይ የጣሉ የቀድሞ ቅዱሳን ሴቶች ራሳቸውን ያስዋቡት በዚህ ዐይነት ለባሎቻቸው በመገዛት ነበርና። 6ሣራም አብርሃምን “ጌታዬ” እያለች ትታዘዘው ነበር፣ እናንተም ምንም ሳትፈሩ መልካም ብታደርጉ የእርሷ ልጆች ናችሁ።

7ባሎች ሆይ፤ እናንተም ደግሞ ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ በኑሯችሁ ሁሉ ለሚስቶቻችሁ ዐስቡላቸው፤ ደካሞች ስለሆኑና የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው።

መልካም በማድረግ መከራን መቀበል

8በመጨረሻም ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። 9ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። 10ስለዚህ፣

“ሕይወትን የሚወድድ፣

መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣

ምላሱን ከክፉ፣

ከንፈሮቹንም ተንኰል ከመናገር ይከልክል።

11ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ፤

ሰላምን ይፈልግ፤ ይከተላትም፤

12ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤

ጆሮቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤

የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው።”

13መልካም ነገር ለማድረግ ብትቀኑ የሚጐዳችሁ ማን ነው? 14ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራ ቢደርስባችሁ ብፁዓን ናችሁ፤ “ዛቻቸውን አትፍሩ3፥14 ወይም የሚፈሩትን አትፍሩ፤ አትታወኩም።” 15ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት። እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁልጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት፤ 16በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጠባይ አክፋፍተው የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ በጎ ኅሊና ይኑራችሁ። 17የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ከሆነ፣ ክፉ ሠርቶ መከራ ከመቀበል ይልቅ መልካም አድርጎ መከራ መቀበል ይሻላል፤ 18እንዲሁም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ኀጢአት ሞቷልና፤ ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ፤ እርሱ በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤ 19በመንፈስም ሄዶ በወህኒ ቤት ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው። 20እነዚህ በወህኒ የነበሩት ነፍሳት ቀድሞ በኖኅ ዘመን መርከብ ሲሠራ እግዚአብሔር በትዕግሥት ይጠብቃቸው የነበሩ እንቢተኞች ናቸው፤ በውሃ የዳኑት ጥቂት፣ ይኸውም ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። 21ይህም ውሃ አሁን የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል፤ ይህም የሰውነትን እድፍ በማስወገድ ሳይሆን በንጹሕ ኅሊና በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ መማፀኛ3፥21 ወይም ምላሽ ነው፤ የሚያድናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካይነት ነው፤ 22እርሱም ወደ ሰማይ ወጥቶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ፤ መላእክትና ሥልጣናት፣ ኀይላትም ተገዝተውለታል።