1 ጴጥሮስ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ጴጥሮስ 2:1-25

1እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን ሁሉ፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ። 2በድነታችሁ እንድታድጉ፣ አዲስ እንደ ተወለዱ ሕፃናት ንጹሑን መንፈሳዊ ወተት ተመኙ፤ 3ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችኋልና።

ሕያው ድንጋይና የተመረጠ ሕዝብ

4በሰው ዘንድ ወደ ተናቀው፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ወደ ተመረጠውና ክቡር ወደ ሆነው ወደዚህ ሕያው ድንጋይ እየቀረባችሁ፣ 5እናንተ ደግሞ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕት ታቀርቡ ዘንድ፣ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ትሠራላችሁ። 6ምክንያቱም በመጽሐፍ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤

“እነሆ፤ የተመረጠና ክቡር የማእዘን ድንጋይ፣

በጽዮን አኖራለሁ፤

በእርሱም የሚያምን ከቶ አያፍርም።”

7እንግዲህ ለእናንተ ለምታምኑት ይህ ድንጋይ ክቡር ነው፤ ለማያምኑት ግን፣

“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣

እርሱ የማእዘን ራስ2፥7 ወይም የማእዘን ድንጋይ ሆነ።”

8ደግሞም፣

“ሰዎችን የሚያሰናክል፣

የሚጥላቸውም ዐለት ሆነ።”

የሚሰናከሉት ቃሉን ባለመታዘዛቸው ነው፤ የተመደቡት ለዚህ ነውና።

9እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ። 10ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።

11ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ። 12ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም፣ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ።

ለአለቆችና ለጌቶች መታዘዝ

13ስለ ጌታ ብላችሁ ለምድራዊ ባለሥልጣን ሁሉ ተገዙ፤ የበላይ ባለሥልጣን ስለሆነ ለንጉሥ ቢሆን፣ 14ወይም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣትና በጎ አድራጊዎችን ለማመስገን እርሱ ለሾማቸው ገዦች ታዘዙ፤ 15ምክንያቱም፣ መልካም በማድረግ የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። 16እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። 17ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ።

18እናንተ አገልጋዮች ሆይ፤ ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን፣ ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ። 19ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል። 20ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ብትቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል። 21የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው።

22“እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤

በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።”

23ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ። 24ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በዕንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቍስል እናንተ ተፈውሳችኋል። 25ቀድሞ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።