1 ጴጥሮስ 4 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ጴጥሮስ 4:1-19

ለእግዚአብሔር መኖር

1እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቷል። 2ከዚህም የተነሣ ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ምኞት አይኖርም። 3አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል። 4ይህን በመሰለ ብኩን ሕይወት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እንግዳ ሆኖባቸው በመደነቅ ይሰድቧችኋል። 5ነገር ግን በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ። 6ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር የተሰበከው በዚህ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋ ይፈረድባቸዋል፤ በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይኖራሉ።

7የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቧል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። 8ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና፣ ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ 9እርስ በርሳችሁ ያለ ማጕረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። 10እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። 11ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

ክርስቲያን በመሆን የሚደርስ መከራ

12ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ 13ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ። 14ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ። 15ከእናንተ ማንም መከራን የሚቀበል ቢኖር፣ ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ወንጀለኛ ወይም በሰው ነገር ጣልቃ ገቢ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ 16ክርስቲያን በመሆኑ መከራ ቢደርስበት ግን፣ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር። 17ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሷልና፤ እንግዲህ ፍርድ የሚጀምረው በእኛ ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ ሰዎች መጨረሻቸው ምን ይሆን? 18እንግዲህ፣

“ጻድቅ የሚድነው በጭንቅ ከሆነ፣

ዐመፀኛውና ኀጢአተኛው እንዴት ሊሆን ይሆን?”

19ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ።