ዕዝራ 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዕዝራ 8:1-36

ከዕዝራ ጋር የተመለሱት የየቤተ ሰቡ አለቆች ስም ዝርዝር

1በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ከባቢሎን አብረውኝ የወጡት የየቤተ ሰቡ አለቆችና አብረዋቸው የተመዘገቡት እነዚህ ናቸው፤

2ከፊንሐስ ዘሮች ጌርሶን፤

ከኢታምር ዘሮች ዳንኤል፤

ከዳዊት ዘሮች ሐጡስ፤ 3እርሱም ከሴኬንያ ዘሮች ነው፤

ከፋሮስ ዘሮች ዘካርያስና ከእርሱም ጋር 150 ወንዶች ተመዝግበው ነበር፤

4ከፋሐት ሞዓብ ዘሮች የዘራእያ ልጅ ኤሊሆ ዔናይና ከእርሱም ጋር 200 ወንዶች፤

5ከዛቱ8፥5 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች (እንዲሁም መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 8፥22) ይህን ስም ይጨምራሉ፤ ዕብራይስጡ ግን ዛቱ የሚለውን አይጨምርም። ዘሮች የየሕዚኤል ልጅ ሴኬንያና ከእርሱም ጋር 300 ወንዶች፤

6ከዓዲን ዘሮች የዮናታን ልጅ ዔቤድና ከእርሱም ጋር 50 ወንዶች፤

7ከኤላም ዘሮች የጎቶልያ ልጅ የሻያና ከእርሱም ጋር 70 ወንዶች፤

8ከሰፋጥያስ ዘሮች፣ የሚካኤል ልጅ ዝባድያ፣ ከ80 ወንዶች ጋር፤

9ከኢዮአብ ዘሮች የይሒኤል ልጅ አብድዩና ከእርሱ ጋር 218 ወንዶች፤

10ከባኒ8፥10 አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች (እንዲሁም መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 8፥36) ይህን ስም ይጨምራሉ፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ባኒ የሚለውን አይጨምርም። ዘሮች የዮሲፍያ ልጅ ሰሎሚትና ከእርሱም ጋር 160 ወንዶች፤

11ከቤባይ ዘሮች የቤባይ ልጅ ዘካርያስ ከእርሱም ጋር 28 ወንዶች፤

12ከዓዝጋድ ዘሮች የሃቃጣን ልጅ ዮሐናንና ከእርሱም ጋር 110 ወንዶች፤

13ከአዶኒቃም ዘሮች፣ የመጨረሻዎቹ ስማቸው ይህ ነው፤ ኤሊፋላት፣ ይዑኤልና ሸማያ፣ ከእነርሱም ጋር 60 ወንዶች፤

14ከበጉዋይ ዘሮች ዑታይና ዘቡድ፣ ከእነርሱም ጋር 70 ወንዶች።

ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ

15እኔም ወደ አኅዋ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ ሰዎቹን ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን ቈየን። ሕዝቡንና ካህናቱን ስመለከት፣ ከሌዊ ወገን የሆነ አንድም ሰው በዚያ አላገኘሁም። 16ስለዚህ መራሕያኑን አልዓዛርን፣ አርኤልን፣ ሸማያን፣ ኤልናታንን፣ ያሪብን፣ ኤልናታን፣ ናታንን፣ ዘካርያስንና ሜሱላምን እንዲሁም መምህራኑን ዮያሪብንና ኤልናታንን አስጠራኋቸው፤ 17እነርሱንም ካሲፍያ በሚባል ስፍራ አለቃ ወደ ሆነው ወደ አዶ ላክኋቸው፤ በአምላካችን ቤት የሚያገለግሉ ሰዎችን ያመጡልን ዘንድ በካሲፍያ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ለሆኑት ለአዶና ለሥጋ ዘመዶቹ የሚናገሩትን አስታወቅኋቸው። 18መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በእኛ ላይ ስለ ነበረች፣ ከሞሖሊ ዘሮች የእስራኤል ልጅ የሌዊ ልጅ የሆነውን ሰራብያ ተብሎ የሚጠራውን አስተዋይ ሰው፣ ከእርሱም ጋር ዐሥራ ስምንት የሚሆኑ ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አመጡልን፤ 19እንዲሁም ሐሸብያንና ከሜራሪ ዘሮች የሻያን፣ ከወንድሞቹና ከአጎቶቹ ወንዶች ልጆች ጋር 20 ወንዶችን አመጡልን። 20በተጨማሪም ዳዊትና ሹማምቱ ሌዋውያኑን እንዲረዳ ካቋቋሙት ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ቡድን 220 አመጡ፤ እነዚህም ሁሉ በየስማቸው ተመዘገቡ።

21ራሳችንን በአምላካችን ፊት ዝቅ እንድናደርግ፣ ጕዞውም ለእኛና ለልጆቻችን፣ ለንብረታችንም ሁሉ የተቃና እንዲሆንልን፣ እዚያው በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅሁ። 22“መልካሚቱ የአምላካችን እጅ በሚፈልጉት ሁሉ ላይ ናት፤ እርሱን በሚተዉ ሁሉ ላይ ግን ቍጣው ትወርድባቸዋለች” ብለን ለንጉሡ ነግረነው ስለ ነበር፣ በመንገድ ላይ ከጠላት የሚጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ንጉሡን ለመጠየቅ ዐፍሬ ነበር። 23ስለዚህ ጾምን፤ ወደ አምላካችንም ስለዚህ ነገር ልመና አቀረብን፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።

24እኔም ከዋና ዋናዎቹ ካህናትም ዐሥራ ሁለት ሰዎችን፣ ከእነርሱም ጋር ሰራብያን፣ ሐሸቢያንና ከወንድሞቻቸውም መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ፤ 25ንጉሡ፣ አማካሪዎቹ፣ ሹሞቹና በዚያ የነበሩ እስራኤል ሁሉ ለአምላካችን ቤት የሰጡትን ብር፣ ወርቅና ዕቃ ሁሉ መዝኜ ሰጠኋቸው። 26ስድስት መቶ አምሳ መክሊት8፥26 22 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ብር፣ አንድ መቶ መክሊት የብር ዕቃዎች፣ አንድ መቶ መክሊት ወርቅ፣8፥26 3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። 27አንድ ሺሕ ዳሪክ8፥27 8.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። የሚያወጡ ሃያ የወርቅ ወጭቶችና እንደ ወርቅ ነጥረው ከሚያብረቀርቅ ናስ የተሠሩ ሁለት ዕቃዎችን መዝኜ በእጃቸው አስረከብኋቸው።

28እንዲህም አልኋቸው፤ “እናንተና እነዚህ ዕቃዎች ለእግዚአብሔር ተቀድሳችኋል፤ ብሩና ወርቁ ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር በበጎ ፈቃድ የቀረበ መባ ነው። 29ኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤት ክፍሎች ውስጥ በዋና ዋናዎቹ ካህናት፣ በሌዋውያኑና በየቤተ ሰቡ የእስራኤል አለቆች ፊት እስክትመዝኗቸው ድረስ በጥንቃቄ ጠብቋቸው።” 30ከዚያም ካህናቱና ሌዋውያኑ ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ አምላካችን ቤት እንዲሄድ የተመዘነውን ብር፣ ወርቅና ንዋያተ ቅድሳት ተረከቡ።

31እኛም በመጀመሪያው ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ከአኅዋ ወንዝ ተነሣን። የአምላካችን እጅ በላያችን ነበረች፤ እርሱም ከጠላቶቻችንና በመንገድ ላይ ከሚሸምቁ አዳነን። 32ኢየሩሳሌምም ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ዐረፍን።

33በአራተኛው ቀን ብሩን፣ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱን በአምላካችን ቤት መዝነን ለኦሪዮ ልጅ ለካህኑ ለሜሪሞት በእጁ አስረከብነው፤ ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር፣ ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ ዮዛባትና የቢንዊ ልጅ ኖዓድያ ነበሩ። 34ሁሉም ነገር ተቈጠረ፤ ተመዘነም፤ የተመዘነውም ሁሉ በዚያኑ ጊዜ ተመዘገበ።

35ከዚያም ከምርኮ የተመለሱት፣ ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት ወይፈኖችን፣ ዘጠና ስድስት አውራ በጎችን፣ ሰባ ሰባት ተባዕት ጠቦቶችን፣ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን አቀረቡ። ይህም ሁሉ ለእግዚአብሔር የቀረበ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበር። 36የንጉሡንም ትእዛዝ ለንጉሡ እንደራሴዎችና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት አገረ ገዦች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት ረዱ።