2 ዜና መዋዕል 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ዜና መዋዕል 1:1-17

ሰሎሞን ጥበብ እንዲሰጠው ጠየቀ

1፥2-13 ተጓ ምብ – 3፥4-15

1፥14-17 ተጓ ምብ – 1ነገ 10፥26-292ዜና 9፥25-28

1አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣ እጅግም ስላገነነው፣ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ ላይ ተደላድሎ ተቀመጠ።

2ከዚያም ሰሎሞን ለመላው እስራኤል፣ ለሻለቆች፣ ለመቶ አለቆች፣ ለዳኞች፣ ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንዲሁም ለየቤተ ሰቡ አለቆች ተናገረ። 3የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የአምላክ የመገናኛ ድንኳን በዚያ ስለ ነበር፣ ሰሎሞንና መላው ጉባኤ በገባዖን ወዳለው ኰረብታ ሄዱ። 4በዚያ ጊዜ ዳዊት የአምላክን ታቦት ከቂሪያት ይዓሪም በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎ ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር፤ 5ይሁን እንጂ የሆር ልጅ፣ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው መሠዊያ በገባዖን በእግዚአብሔር ማደሪያ ድንኳን ፊት ለፊት ይገኝ ነበር፤ ስለዚህ ሰሎሞንና ጉባኤው ይህንኑ ፈለጉ። 6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጥቶ በላዩ ላይ አንድ ሺሕ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

7በዚያ ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ተገልጦ፣ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ሁሉ ጠይቀኝ” አለው።

8ሰሎሞን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ለአባቴ ለዳዊት ታላቅ በጎነት አድርገህለታል፤ እኔንም በእግሩ ተክተህ አንግሠኸኛል። 9አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ያነገሥኸኝ ብዛቱ እንደ ትቢያ በሆነ ሕዝብ ላይ ስለሆነ፣ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና። 10ይህን ሕዝብ ለመምራት እንድችል፣ ጥበብና ዕውቀትን ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ይህን ታላቅ ሕዝብህን ማን ሊገዛ ይችላል?”

11እግዚአብሔርም ሰሎሞንን እንዲህ አለው፤ “የልብህ መሻት ይህ ስለሆነ፣ ብልጽግናና ሀብት ወይም የጠላቶችህን ነፍስ ወይም ረዥም ዕድሜ ስላልጠየቅህ፣ ነገር ግን ባነገሥሁህ ሕዝቤ ላይ የምትገዛበትን ጥበብና ዕውቀት ስለ ጠየቅህ፣ 12ጥበብና ዕውቀት ይሰጥሃል፤ እንዲሁም ከአንተ በፊት የነበረ ማንኛውም ንጉሥ ያላገኘውን፣ ከአንተ በኋላም የሚነሣው የማያገኘውን ብልጽግና፣ ሀብትና ክብር እሰጥሃለሁ።”

13ሰሎሞንም የመገናኛው ድንኳን ካለበት ከገባዖን ኰረብታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።

14ሰሎሞን ሠረገሎችንና1፥14 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ፈረሶችን ሰበሰበ፤ እርሱም አንድ ሺሕ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት፤ እነርሱንም በሠረገላ ከተሞችና እርሱ ባለበት በኢየሩሳሌም ከተማ አኖራቸው። 15ንጉሡም ወርቁና ብሩ በኢየሩሳሌም እንደ ተራ ድንጋይ እንዲበዛ፣ ዝግባውም በየኰረብታው ግርጌ እንደሚገኝ የሾላ ዛፍ እንዲበዛ አደረገ። 16የሰሎሞንም ፈረሶች የመጡት ከግብፅና ከቀዌ1፥16 ምናልባት ኪልቂያ ናት ነበር፤ ከቀዌ የገዟቸውም የንጉሡ ነጋዴዎች ነበሩ። 17ከግብፅ ያስገቧቸውም አንዱን ሠረገላ በስድስት መቶ ሰቅል1፥17 7 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር፣ አንዱን ፈረስ በአንድ መቶ አምሳ ሰቅል1፥17 1.7 ኪሎ ግራም ነው። ብር ገዝተው ነው። እነዚህንም ደግሞ ለኬጢያውያንና ለሶርያውያን ነገሥታት ሁሉ ይሸጡላቸው ነበር።