ዕዝራ 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዕዝራ 7:1-28

ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ

1ከእነዚህም ነገሮች በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት፣ ዕዝራ የሠራያ ልጅ፣ የዓዛርያስ ልጅ፣ የኬልቅያስ ልጅ 2የሰሎም ልጅ፣ የሳዶቅ ልጅ፣ የአኪጦብ ልጅ፣ 3የአማርያ ልጅ፣ የዓዛርያስ ልጅ፣ የመራዮት ልጅ፣ 4የዘራእያ ልጅ፣ የኦዚ ልጅ፣ የቡቂ ልጅ፣ 5የአቢሱ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ፣ የአልዓዛር ልጅ፣ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፤ 6ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ሕግ በሚገባ የሚያውቅ የሕግ መምህር ነበር። የአምላኩ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ የጠየቀውን ሁሉ ንጉሡ ፈቀደለት። 7እንደዚሁም አንዳንድ እስራኤላውያን፣ ከካህናት፣ ከሌዋውያን፣ ከመዘምራን፣ ከበር ጠባቂዎችና ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ጋር በመሆን በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሰባተኛው ዓመት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

8ዕዝራ በንጉሡ ሰባተኛ ዓመት በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ደረሰ። 9መልካሚቱ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ኢየሩሳሌም ደረሰ። 10ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በማድረግ፣ ለእስራኤልም ሥርዐቱንና ሕጉን በማስተማር ራሱን ፈጽሞ ሰጥቶ ነበር።

ንጉሥ አርጤክስስ ለዕዝራ የሰጠው ደብዳቤ

11እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠውን ሕግና ትእዛዝ ዐዋቂ ለነበረው ለካህኑና ለመምህሩ ዕዝራ ንጉሥ አርጤክስስ የሰጠው የደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

127፥12 ዕዝ 7፥12-26 ላይ የሚገኘው ክፍል የተጻፈው በአረማይክ ቋንቋ ነው። ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፤ ለሰማይ አምላክ ሕግ መምህር ለሆነው ለካህኑ ለዕዝራ፤

ሰላም ለአንተ ይሁን፤

13ካህናቱንና ሌዋውያኑን ጨምሮ በመንግሥቴ ውስጥ የሚኖርና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚፈልግ ማንኛውም እስራኤላዊ መሄድ እንዲችል ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። 14በእጅህ በሚገኘው በአምላክህ ሕግ መሠረት፣ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል። 15ከዚህም በላይ፣ ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤ 16እንዲሁም ከመላው ባቢሎን አውራጃ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፣ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ በፈቃዳቸው የሚሰጡትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ። 17በዚህም ገንዘብ ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን፣ ከእህል ቍርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቍርባኖቻቸው ጋር መግዛት እንዳለብህ አትርሳ፤ እነዚህንም በኢየሩሳሌም በሚገኘው በአምላካችሁ ቤተ መቅደስ መሠዊያ ላይ አቅርብ። 18ከዚህ የሚቀረውንም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ አይሁድ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ደስ ለሚላችሁ ነገር ሁሉ አውሉት። 19ለአምላክህ ቤተ መቅደስ በዐደራ የተሰጠህንም ዕቃ ሁሉ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ። 20ከዚህም በላይ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ለመስጠት የምትፈልገውን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ግምጃ ቤት መውሰድ ትችላለህ።

21በኤፍራጥስ ማዶ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ፣ የሰማይ አምላክ ሕግ መምህር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት እኔ ንጉሥ አርጤክስስ እነሆ አዝዣለሁ፤ 22እስከ አንድ መቶ መክሊት7፥22 3.4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ብር፣ እስከ አንድ መቶ ቆሮስ7፥22 22 ኪሎ ሊትር ያህል ነው። ስንዴ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ7፥22 2.2 ኪሎ ሊትር ያህል ነው። መስፈሪያ ወይን ጠጅ፣ እስከ አንድ መቶ ባዶስ የወይራ ዘይትና የሚፈለገውን ያህል ጨው ስጡት። 23የሰማይ አምላክ የሚያዘው ሁሉ፣ ለሰማይ አምላክ ቤተ መቅደስ በፍጹም ትጋት ይደረግ፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ለምን ቍጣ ይውረድ? 24ደግሞም በካህናቱ፣ በሌዋውያኑ፣ በመዘምራኑ፣ በበር ጠባቂዎቹ፣ በቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ወይም በሌሎቹ በዚህ በእግዚአብሔር ቤት ሠራተኞች ላይ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻ ለመጣል ሥልጣን እንደሌላችሁ ይህን ዕወቁ።

25አንተም ዕዝራ ከአምላክህ እንደ ተሰጠህ ጥበብ መጠን፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ለሚገኙት ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ የሚያውቁ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፤ ሕጉን የማያውቅ ሰው ቢኖር፣ አንተ ራስህ አስተምረው። 26ለአምላክህ ሕግና ለንጉሡ ሕግ የማይታዘዝ ማንኛውም ሰው፣ የሞት ወይም የስደት ወይም የንብረት መወረስ ወይም የእስራት ቅጣት ይፈጸምበት።

27በኢየሩሳሌም የሚገኘው የእግዚአብሔር ቤት በዚህ ሁኔታ እንዲከበር ይህን በንጉሡ ልብ ያኖረ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ቡሩክ ይሁን፤ 28እንዲሁም በንጉሡ፣ በአማካሪዎቹና በኀያላን ሹሞቹ ፊት ሁሉ ሞገስን የሰጠኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን። የአምላኬ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ስለ ነበረች፣ አብረውኝ እንዲሄዱ ከእስራኤል መካከል የታወቁ ሰዎችን ለመሰብሰብ ብርታት አገኘሁ።