ዕንባቆም 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዕንባቆም 1:1-17

1ነቢዩ ዕንባቆም የተቀበለው ንግር፤

የዕንባቆም ማጕረምረም

2እግዚአብሔር ሆይ፤ ለርዳታ እየተጣራሁ፣

አንተ የማትሰማው እስከ መቼ ነው?

“ግፍ በዛ” ብዬ እየጮኽሁ፣

አንተ የማታድነው እስከ መቼ ነው?

3ስለ ምን በደልን እንዳይ አደረግኸኝ?

እንዴትስ ግፍ ሲፈጸም ትታገሣለህ?

ጥፋትና ግፍ በፊቴ አለ፤

ጠብና ግጭት በዝቷል።

4ስለዚህ ሕግ ላልቷል፤

ፍትሕ ድል አይነሣም፤

ፍትሕ ይጣመም ዘንድ፣

ክፉዎች ጻድቃንን ይከብባሉ።

የእግዚአብሔር መልስ

5“ቢነገራችሁም እንኳ፣

የማታምኑትን እናንተን፣

በዘመናችሁ አንድ ነገር ስለማደርግ፣

እነሆ፤ ሕዝቡን እዩ፤ ተመልከቱም፤

እጅግም ተደነቁ።

6የራሳቸው ያልሆኑትን መኖሪያ ስፍራዎች ለመያዝ፣

ምድርን ሁሉ የሚወርሩትን፣

ጨካኝና ፈጣን የሆኑትን፣

ባቢሎናውያንን1፥6 ከለዳውያን ማለት ነው። አስነሣለሁ።

7እነርሱም የሚያስፈሩና የሚያስደነግጡ ናቸው፤

ፍርዳቸውና ክብራቸው፣

ከራሳቸው ይወጣል።

8ፈረሶቻቸው ከነብር ይልቅ ፈጣኖች፣

ከማታም ተኵላ ይልቅ ጨካኞች ናቸው።

ፈረሰኞቻቸው በፍጥነት ይጋልባሉ፤

ከሩቅ ስፍራም ይመጣሉ።

ነጥቆ ለመብላት እንደሚቸኵል አሞራ ይበርራሉ፤

9ሁሉም ለዐመፅ ታጥቀው ይመጣሉ።

ሰራዊታቸው1፥9 የዕብራይስጡ ቃል ትርጕም በትክክል አይታወቅም። እንደ ምድረ በዳ ነፋስ ወደ ፊት ይገሠግሣል፤

ምርኮኞችንም እንደ አሸዋ ይሰበስባል።

10ነገሥታትን ይንቃል፤

በገዦችም ላይ ያፌዛል፤

በምሽግ ሁሉ ላይ ይሥቃል፤

የዐፈር ቍልል ሠርቶም ይይዘዋል።

11ከዚያም በኋላ እንደ ነፋስ ዐልፎ ይሄዳል፤

ጕልበታቸውን አምላካቸው ያደረጉ በደለኞች ናቸው።”

የዕንባቆም ዳግመኛ ማጕረምረም

12እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዘላለም ጀምሮ ያለህ አይደለህምን?

የእኔ አምላክ፣ የእኔ ቅዱስ እኛ አንሞትም፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲፈርዱ ሾመሃቸዋል፤

ዐለት ሆይ፤ ይቀጡ ዘንድ ሥልጣን ሰጠሃቸው።

13ዐይኖችህ ክፉውን እንዳያዩ እጅግ ንጹሓን ናቸው፤

አንተ በደልን መታገሥ አትችልም፤

ታዲያ፣ አታላዮችን ለምን ትታገሣለህ?

ክፉው ከራሱ ይልቅ ጻድቅ የሆነውን ሲውጠውስ፣

ለምን ዝም ትላለህ?

14አንተ ሰዎችን በባሕር ውስጥ እንዳለ ዓሣ፣

ገዥ እንደሌላቸውም የባሕር ፍጥረታት አደረግህ።

15ክፉ ጠላት ሁሉንም በመንጠቆ ያወጣቸዋል፤

በመረቡ ይይዛቸዋል፤

በአሽክላው ውስጥ ይሰበስባቸዋል፤

በዚህም ይደሰታል፤ ሐሤትም ያደርጋል።

16በእነርሱ ተዝናንቶ ይኖራልና፤

ምግቡም ሠብቷል።

ስለዚህ ለመረቡ ይሠዋል፤

ለአሽክላውም ያጥናል።

17ታዲያ መረቡን ባለማቋረጥ መጣል፣

ሕዝቦችንስ ያለ ርኅራኄ መግደል አለበትን?