ናሆም 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ናሆም 1:1-15

1ስለ ነነዌ ጥፋት የተነገረ ንግር፤ የኤልቆሻዊው የናሆም የራእዩ መጽሐፍ ይህ ነው፤

በነነዌ ላይ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቍጣ

2እግዚአብሔር ቀናተኛና ተበቃይ አምላክ ነው፤

እግዚአብሔር የሚበቀል፣ በመዓትም የተሞላ ነው።

እግዚአብሔር ባላጋራዎቹን ይበቀላል፤

በጠላቶቹም ላይ ቍጣውን ያመጣል።

3እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ በኀይሉም ታላቅ ነው፤

እግዚአብሔር በደለኛውን ሳይቀጣ አያልፍም፤

መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በማዕበል ውስጥ ነው፤

ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።

4ባሕርን ይገሥጻል፤ ያደርቀዋልም፤

ወንዞችን ሁሉ ያደርቃል።

ባሳንና ቀርሜሎስ ጠውልገዋል፤

የሊባኖስም አበቦች ረግፈዋል።

5ተራሮች በፊቱ ታወኩ፤

ኰረብቶችም ቀለጡ።

ምድር በፊቱ፣

ዓለምና በውስጧ የሚኖሩት ሁሉ ተናወጡ።

6ቍጣውን ማን ሊቋቋም ይችላል?

ጽኑ ቍጣውንስ ማን ሊሸከም ይችላል?

መዓቱ እንደ እሳት ፈስሷል፤

ዐለቶችም በፊቱ ተሰነጣጥቀዋል።

7እግዚአብሔር መልካም ነው፤

በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው።

ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል፤

8ነነዌን ግን፣

በሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ያጠፋታል፤

ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል።

9በእግዚአብሔር ላይ ምንም ቢያሤሩ1፥9 በእግዚአብሔር ላይ የምታሤሩት ምንድን ነው? የሚሉ አሉ።

እርሱ ያጠፋዋል፤

መከራም ዳግመኛ አይነሣም።

10በእሾኽ ይጠላለፋሉ፤

በወይን ጠጃቸውም ይሰክራሉ፤

እሳትም እንደ ገለባ1፥10 የዕብራይስጡ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ይበላቸዋል።

11ነነዌ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር፣

ክፋትንም የሚመክር፣

ከአንቺ ዘንድ ወጥቷል።

12እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ምንም ኀይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም፣

ይቈረጣሉ፤ ይጠፋሉም።

ይሁዳ ሆይ፤ ከዚህ በፊት ባስጨንቅህም፣

ከእንግዲህ አላስጨንቅህም።

13አሁንም ቀንበራቸውን ከዐንገትህ ላይ አንሥቼ እሰብራለሁ፤

የታሰርህበትንም ሰንሰለት በጥሼ እጥላለሁ።”

14አንቺ ነነዌ፤ እግዚአብሔር ስለ አንቺ እንዲህ ብሎ አዝዟል፤

“ስም የሚያስጠራ ትውልድ አይኖራችሁም፤

በአማልክታችሁ ቤት ያሉትን፣

የተቀረጹትን ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩትን ጣዖታት እደመስሳለሁ፤

መቀበሪያህን እምስልሃለሁ፤

አንተ ክፉ ነህና።”

15እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣው፣

ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣

በተራሮች ላይ ነው፤

ይሁዳ ሆይ፤ በዓላትህን አክብር፤

ስእለትህንም ፈጽም፤

ከእንግዲህ ክፉዎች አይወርሩህም፤

እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ።