ናሆም 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ናሆም 2:1-13

የነነዌ አወዳደቅ

1ነነዌ ሆይ፤ አጥቂ መጥቶብሻል፤

ምሽግሽን ጠብቂ፤

መንገድሽን ሰልዪ፤

ወገብሽን ታጠቂ፤

ኀይልሽን ሁሉ አሰባስቢ።

2አጥፊዎች ባድማ ቢያደርጓቸውም፣

የወይን ተክል ቦታቸውን ቢያጠፉባቸውም፣

እንደ እስራኤል ክብር ሁሉ፣

እግዚአብሔር የያዕቆብንም ክብር ይመልሳል።

3የወታደሮቹ ጋሻ ቀይ ነው፤

ተዋጊዎቹ ቀይ ልብስ ለብሰዋል፤

ዝግጁ በሆኑበት ቀን፣

የሠረገሎቹ ብረት ያብረቀርቃል፤

የጦሩ ዘንግ ይወዛወዛል2፥3 የዕብራይስጡ ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናቱና የሱርስቱ ቅጆች ግን ፈረሰኞች ይፈጥናሉ ይላሉ።

4ሠረገሎች በአደባባይ ወዲያ ወዲህ ይከንፋሉ፤

በመንገዶችም ላይ ይርመሰመሳሉ፤

የሚንበለበል ፋና ይመስላሉ፤

እንደ መብረቅም ይወረወራሉ።

5ምርጥ ተዋጊዎቹን ይጠራል፤

ዳሩ ግን መንገድ ላይ ይሰናከላሉ፤

ወደ ከተማዪቱ ቅጥር ይሮጣሉ፤

መከላከያ ጋሻውም በቦታው አለ።

6የወንዙ በር ወለል ብሎ ተከፈተ፤

ቤተ መንግሥቱም ወደቀ።

7ከተማዪቱ መማረኳና መወሰዷ እንደማይቀር፣

አስቀድሞ ተነግሯል2፥7 የዕብራይስጡ ቃል ትርጕም በትክክል አይታወቅም።

ሴቶች ባሪያዎቿ እንደ ርግብ ያለቅሳሉ፤

ደረታቸውንም ይደቃሉ።

8ነነዌ እንደ ኵሬ ናት፤

ውሃዋም ይደርቃል፤

“ቁም! ቁም!” ብለው ይጮኻሉ፤

ነገር ግን ወደ ኋላ የሚመለስ የለም።

9ብሩን ዝረፉ!

ወርቁን ንጠቁ!

በየግምጃ ቤቱ ያለው፣

የተከማቸውም ሀብት ስፍር ቍጥር የለውም።

10ተበዝብዛለች፤ ተዘርፋለች፤ ተራቍታለች።

ልብ ቀልጧል፤ ጕልበት ተብረክርኳል፤

ሰውነት ተንቀጥቅጧል፤ ፊት ሁሉ ገርጥቷል።

11አሁን ታዲያ የአንበሶቹ ዋሻ፣

ደቦሎቻቸውን ያበሉበት

ወንዱና ሴቷ አንበሳ የሄዱበት፣

ግልገሎችም ሳይፈሩ የተሰማሩበት ቦታ ወዴት ነው?

12አንበሳው ለግልገሎቹ የሚበቃውን ያህል ገደለ፤

ለእንስቶቹም ዐንቆ ገደለላቸው፤

የገደለውን በማረፊያ ቦታው፣

የነጠቀውንም በዋሻው ሞልቶታል።

13የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“በእናንተ ላይ ተነሥቼባችኋለሁ፤

ሠረገሎቻችሁን አቃጥዬ አጨሳለሁ፤

ደቦል አንበሶቻችሁን ሰይፍ ይበላል፤

የምትበሉትን በምድር ላይ አልተውላችሁም፤

የመልእክተኞቻችሁም ድምፅ፣

ከእንግዲህ ወዲያ አይሰማም።”