ማርቆስ 9 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 9:1-50

1ቀጥሎም፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔር መንግሥት በኀይል ስትመጣ እስከሚያዩ ድረስ ሞትን የማይቀምሱ አንዳንዶች አሉ” አላቸው።

የኢየሱስ መልክ አበራ

9፥2-8 ተጓ ምብ – ሉቃ 9፥28-36

9፥2-13 ተጓ ምብ – ማቴ 17፥1-13

2ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረዥም ተራራ ይዟቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤ 3ልብሱም በምድር ላይ ማንም ዐጣቢ ዐጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። 4ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

5ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። 6እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር።

7ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ።

8ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም።

9ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። 10እነርሱም የተናገራቸውን ቃል በልባቸው አሳደሩት፤ ነገር ግን፣ “ከሙታን መነሣት” ምን ማለት እንደ ሆነ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።

11ከዚያም፣ “ጸሐፍት አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ጠየቁት።

12ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ኤልያስ በርግጥ አስቀድሞ መጥቶ ሁሉን ነገር እንደ ነበረ ያደርጋል፤ ታዲያ፣ የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበልና መናቅ እንዳለበት የተጻፈው ለምን ይመስላችኋል? 13ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ኤልያስማ መጥቶ ነበር፤ እነርሱም ስለ እርሱ በተጻፈው መሠረት ያሻቸውን ሁሉ አድርገውበታል።”

ርኩስ መንፈስ ያለበት ልጅ ተፈወሰ

9፥14-283032 ተጓ ምብ – ማቴ 17፥14-1922-23ሉቃ 9፥37-45

14ወደ ቀሩት ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ሲመጡ፣ ብዙ ሕዝብ ከብበዋቸው፣ ጸሐፍት ከእነርሱ ጋር ሲከራከሩ አዩ። 15ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩት ወዲያው ተደንቀው እጅ ሊነሡት ወደ እርሱ ሮጡ።

16እርሱም፣ “ከእነርሱ ጋር የምትከራከሩት ስለ ምን ጕዳይ ነበር” ሲል ጠየቃቸው።

17ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ 18በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።”

19ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው።

20ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር።

21ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው።

እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ 22ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።”

23ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው።

24ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ።

25ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን9፥25 ወይም ክፉ መንፈስ ገሠጸው።

26ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። 27ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ።

28ኢየሱስ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው፣ “እኛ ልናስወጣው ያልቻልነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት።

29እርሱም፣ “የዚህ ዐይነቱ ሊወጣ የሚችለው በጸሎትና በጾም9፥29 አንዳንድ ቅጆች በጾም የሚለው የላቸውም። ብቻ ነው” አላቸው።

30ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል ዐለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ 31ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። 32እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው?

9፥33-37 ተጓ ምብ – ማቴ 18፥1-5ሉቃ 9፥46-48

33ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም፣ “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለ ምን ነበር?” ብሎ ጠየቃቸው። 34እነርሱ ግን በመንገድ ላይ የተከራከሩት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ነው በሚል ስለ ነበር ዝም አሉ።

35ከተቀመጠ በኋላ ዐሥራ ሁለቱን ጠርቶ፣ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ፣ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው።

36ትንሽ ልጅ አምጥቶም በመካከላቸው አቆመ፤ ዐቅፎትም፣ 37“ከእነዚህ ሕፃናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው።

የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው

9፥38-40 ተጓ ምብ – ሉቃ 9፥4950

38ዮሐንስም፣ “መምህር ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፣ እኛን ስለማይከተልም ከለከልነው” አለው።

39ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ፤ “አትከልክሉት፤ ማንም በስሜ ታምር ሠርቶ ወዲያውኑ በእኔ ላይ ክፉ መናገር አይችልም፤ 40የማይቃወመን ሁሉ ከእኛ ጋር ነውና፤ 41እውነት እላችኋለሁ፣ የክርስቶስ በመሆናችሁ በስሜ አንድ ኩባያ ውሃ የሚሰጣችሁ ሁሉ ዋጋውን አያጣም።

ለሌላው መሰናክል መሆን

42“በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል። 43ስለዚህ እጅህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እጅ ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመሄድ፣ ጕንድሽ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ 44በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና9፥44 እነዚህ ጥቅሶች በአንዳንድ ቅጆች አይገኙም። 45እግርህ ብታሰናክልህ ቍረጣት፤ ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ ዐንካሳ ሆነህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል፤ 46በገሃነም ትሉ አይሞትም፤ እሳቱ አይጠፋምና9፥46 እነዚህ ጥቅሶች በአንዳንድ ቅጆች አይገኙም። 47ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጕለህ አውጣት፤ ሁለት ዐይን ኖሮህ ወደ ገሃነም ከመጣል፣ አንድ ዐይን ኖሮህ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ይሻልሃል፤

48“በገሃነም ትሉ አይሞትም፤

እሳቱ አይጠፋምና፤

49ሰው ሁሉ በእሳት ይቀመማልና።

50“ጨው መልካም ነው፤ ነገር ግን ጨው ጨውነቱን ቢያጣ እንዴት መልሳችሁ ጣዕም እንዲኖረው ታደርጉታላችሁ? ጨው በውስጣችሁ ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም ተስማሙ።”