ማቴዎስ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማቴዎስ 1:1-25

የኢየሱስ የትውልድ ሐረግ

1፥1-17 ተጓ ምብ – ሉቃ 3፥23-38

1፥3-6 ተጓ ምብ – ሩት 4፥18-22

1፥7-11 ተጓ ምብ – 1ዜና 3፥10-17

1የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ የሚከተለው ነው።

2አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤

ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤

ያዕቆብ ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤

3ይሁዳ ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤

ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፤

ኤስሮምም አራምን ወለደ፤

4አራም አሚናዳብን ወለደ፤

አሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤

ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤

5ሰልሞን ቦዔዝን ከረዓብ ወለደ፤

ቦዔዝ ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤

ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤

6እሴይ ንጉሥ ዳዊትን ወለደ።

ዳዊት የኦርዮ ሚስት ከነበረችው ሰሎሞንን ወለደ፤

7ሰሎሞን ሮብዓምን ወለደ፤

ሮብዓም አቢያን ወለደ፤

አቢያም አሣፍን ወለደ፤

8አሣፍ ኢዮሣፍጥን ወለደ፤

ኢዮሣፍጥ ኢዮሆራምን ወለደ፤

ኢዮሆራም ዖዝያንን ወለደ፤

9ዖዝያን ኢዮአታምን ወለደ፤

ኢዮአታም አካዝን ወለደ፤

አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤

10ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤

ምናሴ አሞንን ወለደ፤

አሞንም ኢዮስያስን ወለደ፤ 11ኢዮስያስ በባቢሎን ምርኮ ጊዜ፣

ኢኮንያንንና1፥11 ዮአኪን ማለት ነው፤ 12 ይመ ወንድሞቹን ወለደ።

12ከባቢሎን ምርኮ በኋላ፣

ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤

ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ፤

13ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤

አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤

ኤልያቄም አዛርን ወለደ፤

14አዛር ሳዶቅን ወለደ፤

ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤

አኪምም ኤልዩድን ወለደ፤

15ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤

አልዓዛር ማታንን ወለደ፤

ማታን ያዕቆብን ወለደ፤

16ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ፤ ዮሴፍም የኢየሱስ ክርስቶስ እናት የማርያም ዕጮኛ ነበር።

17እንግዲህ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፣ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፣ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ1፥17 ወይም መሲሕ “ክርስቶስ” (በግሪክ) እና “መሲሕ” (በዕብራይስጥ) ሁለቱም “የተቀባው” የሚል ትርጕም አላቸው። ልደት ዐሥራ አራት ትውልድ ይሆናል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት

18የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። 19ዕጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለ ነበርና ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ።

20በዚህ ሐሳብ ሳለ፣ የጌታ መልአክ በሕልም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ ዕጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና። 21ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ1፥21 ኢየሱስ በግሪኩ ሲሆን በዕብራይስጡ ኢያሱ ነው፤ ትርጕሙም እግዚአብሔር ያድናል ማለት ነው ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና።”

22ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤ 23“እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ይሉታል፤” ትርጕሙም፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ማለት ነው።

24ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ እንዳዘዘው ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት።1፥24 ወደ ቤቱ ወሰዳት የሚለው የግሪኩ ቃል ሚስቱ እንድትሆን ወሰዳት ይለዋል። 25ይሁን እንጂ የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ የተወለደውንም ሕፃን፣ “ኢየሱስ” ብሎ ጠራው።