ሚልክያስ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሚልክያስ 1:1-14

1በሚልክያስ1፥1 ሚልክያስ የስሙ ትርጕም መልእክተኛዬ ማለት ነው። በኩል ወደ እስራኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ንግር ይህ ነው፤

ያዕቆብ ተወደደ፤ ዔሳው ተጠላ

2“እኔ ወድጃችኋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “እናንተ ግን፣ ‘እንዴት ወደድኸን?’ ትላላችሁ።”

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን? ያዕቆብን ወደድሁት፤ 3ዔሳውን ግን ጠላሁት፤ ተራሮቹን ባድማ አደረግሁ፤ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮዎች ሰጠሁበት።”

4ኤዶምያስ፣ “ብንደመሰስም እንኳ የፈረሰውን መልሰን እንሠራዋለን” ይል ይሆናል። እግዚአብሔር ጸባኦት ግን እንዲህ ይላል፤ “እነርሱ ይሠሩ ይሆናል፤ እኔ ግን አፈርስባቸዋለሁ፤ ክፉ ምድር፣ እግዚአብሔርም ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ። 5ይህንም በገዛ ዐይናችሁ ታያላችሁ፤ እናንተም፣ ‘ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ እንኳ እግዚአብሔር ታላቅ ነው!’ ትላላችሁ።

እንከን ያለበት መሥዋዕት

6“ልጅ አባቱን፣ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔ አባት ከሆንሁ፣ መከበሬ የት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ የት አለ?” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ካህናት ሆይ፤ ስሜን የምታቃልሉት እናንተ ናችሁ።

“እናንተ ግን፣ ‘ስምህን ያቃለልነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ።

7“በመሠዊያዬ ላይ የረከሰ ምግብ ታስቀምጣላችሁ።

“እናንተ ግን፣ ‘ያረከስንህ እንዴት ነው?’ አላችሁ።

የእግዚአብሔር ገበታ የተናቀ ነው በማለታችሁ ነው። 8የታወረውን እንስሳ ለመሥዋዕት ስታቀርቡ፣ ያ በደል አይደለምን? ዐንካሳውን ወይም በሽተኛውን እንስሳ መሥዋዕት አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ያስ በደል አይደለምን? ያንኑ ለገዣችሁ ብታቀርቡ፣ በእናንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ይቀበለዋልን?” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

9“አሁን ግን እንዲራራልን እግዚአብሔርን ለምኑ፤ እንደዚህ ዐይነቱን መሥዋዕት ይዛችሁ ስትቀርቡ ይቀበላችኋልን?” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። 10“በመሠዊያዬ ላይ ከንቱ እሳት እንዳታነድዱ፣ ምነው ከእናንተ አንዱ የቤተ መቅደሱን ደጅ በዘጋ ኖሮ! እኔ በእናንተ ደስ አይለኝም፤ ከእጃችሁም ምንም ዐይነት ቍርባን አልቀበልም” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። 11“ከፀሓይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፣ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናል፤ በየስፍራውም ሁሉ ለስሜ ዕጣንና ንጹሕ ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በሕዝቦች መካከል የከበረ ይሆናልና” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

12“እናንተ ግን የእግዚአብሔር ገበታ፣ ‘ርኩስ ነው’ ምግቡም፣ ‘የተናቀ ነው’ በማለት ታቃልላላችሁ። 13ደግሞም፣ ‘ይህ ድካም ነው’ በማለት በንቀት ጢቅ አላችሁበት” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

“በቅሚያ የመጣውን፣ ዐንካሳውንና የታመመውን እንስሳ ቍርባን አድርጋችሁ ስታቀርቡ ከእጃችሁ መቀበል ይገባኛልን?” ይላል እግዚአብሔር14“በመንጋው ውስጥ ተቀባይነት ያለው ተባዕት በግ ኖሮት ይህንኑ ሊሰጥ ተስሎ ሳለ፣ በማታለል ነውር ያለበትን እንስሳ ለጌታ የሚሠዋ ርጉም ይሁን፤ እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝ፤ ስሜም በሕዝቦች ዘንድ ሊፈራ የሚገባ ነውና” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።