ማርቆስ 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 10:1-52

የባልና የሚስት ፍች

10፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥1-9

1ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው።

2አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።

3እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው።

4እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍች ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉ።

5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። 6ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። 7ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል10፥7 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ከሚስቱ ጋር ይጣመራል የሚለው የላቸውም።8ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ 9ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየው።”

10እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። 11እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤ 12እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።

ኢየሱስ ሕፃናትን ባረከ

10፥13-16 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥13-15ሉቃ 18፥15-17

13ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። 14ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 15እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” 16ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።

ሀብታሙ ወጣት

10፥17-31 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥16-30ሉቃ 18፥18-30

17ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጕልበቱ ተንበርክኮ፣ “ቸር መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው።

18ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ለምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ቸር የለም፤ 19ትእዛዞችን ታውቃለህ፤ አትግደል፤ አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ በሐሰት አትመስክር፤ አታታልል፤ አባትህንና እናትህን አክብር።”

20ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው።

21ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሽጥ፤ ለድኾችም ስጥ፤ በሰማይ የተከማቸ ሀብት ታገኛለህ፤ ከዚያ በኋላ ና፤ ተከተለኝም” አለው።

22ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ ዐዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረውም እየተከዘ ሄደ።

23ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው!” አላቸው።

24ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ10፥24 አንዳንድ ቅጆች በሀብት ለሚታመኑ የሚል ሐረግ አላቸው።፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ከባድ ነገር ነው! 25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀልለዋል።”

26ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።

27ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” አላቸው።

28ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” አለው።

29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣ 30አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም። 31ነገር ግን ብዙ ፊተኞች የሆኑ ኋለኞች፣ ኋለኞች የሆኑም ፊተኞች ይሆናሉ።”

ኢየሱስ ዳግም ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ

10፥32-34 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥17-19ሉቃ 18፥31-33

32ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ 33እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ 34ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”

የያዕቆብና የዮሐንስ ጥያቄ

10፥35-45 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥20-28

35ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።

36እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።

37እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት።

38ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።

39እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት።

ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው።

41ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ። 42ኢየሱስም በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ አለቆች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፤ ሹሞቻቸውም በእነርሱ ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ ታውቃላችሁ፤ 43በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ 44ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 45የሰው ልጅ ሊያገለግልና ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ መጣ እንጂ ሊገለገል አልመጣምና።”

ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን ፈወሰ

10፥46-52 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥29-34ሉቃ 18፥35-43

46ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 47እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።

48ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ።

49ኢየሱስም ቆም ብሎ፣ “ጥሩት” አላቸው።

እነርሱም ዐይነ ስውሩን፣ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል!” አሉት። 50እርሱም ልብሱን ጥሎ ብድግ በማለት፣ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ።

51ኢየሱስም፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው።

ዐይነ ስውሩም፣ “መምህር ሆይ፤ እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው።

52ኢየሱስም፣ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ።