ማርቆስ 15 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 15:1-47

ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት

15፥2-15 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥11-26ሉቃ 23፥2318-25ዮሐ 18፥29–19፥16

1ጧት በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሓፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋር ወዲያው ከተማከሩ በኋላ፣ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።

2ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?”

ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፣ “አንተው አልኸው፣” በማለት መለሰለት።

3የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። 4ጲላጦስም፣ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ፤ በብዙ ነገር ከስሰውሃል” ሲል እንደ ገና ጠየቀው።

5ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ።

6በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። 7በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። 8ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ጲላጦስን ለመኑት።

9ጲላጦስም፣ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ 10ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። 11የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ።

12ጲላጦስም እንደ ገና፣ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።

13እነርሱም እንደ ገና፣ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።

14ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ” አላቸው።

እነርሱ ግን፣ “ስቀለው!” እያሉ የባሰ ጮኹ።

15ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

ወታደሮች በኢየሱስ ላይ አፌዙ

15፥16-20 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥27-31

16ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ። 17ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት። 18ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤ 19ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። 20ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

የኢየሱስ ስቅለት

15፥22-32 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥33-44ሉቃ 23፥33-43ዮሐ 19፥17-24

21የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት። 22ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጕሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት። 23ከከርቤ ጋር የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም። 24ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ።

25ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ነበረ። 26የክሱ ጽሑፍም፣ “የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር። 27ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። 28መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ።15፥28 አንዳንድ ቅጆች 28 የላቸውም (ኢሳ 53፥12)። 29በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዬ! ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ አንተ ነህ፤ 30እስቲ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን።”

31እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም፤ 32አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ15፥32 ወይም መሲሕ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስቲ ከመስቀል ይውረድ።” ከእርሱ ጋር የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።

የኢየሱስ መሞት

15፥33-41 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥45-56ሉቃ 23፥44-49

33ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ። 34በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።

35በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ።

36ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የሆመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስቲ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ።

37ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ።

38የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ። 39በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ15፥39 አንዳንድ ቅጆች እንደዚህ ጮኾ የሚለው ሐረግ የላቸውም። ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ።

40በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤ 41እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም አብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ።

የኢየሱስ መቀበር

15፥42-47 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥57-61ሉቃ 23፥50-56ዮሐ 19፥38-42

42ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤ 43የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው። 44ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሆነ ጠየቀው፤ 45መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው። 46ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው። 47ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።