ማርቆስ 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 14:1-72

ኢየሱስን ሽቶ የቀባችው ሴት

14፥1-11 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥2-16

14፥121011 ተጓ ምብ – ሉቃ 22፥1-6

14፥3-8 ተጓ ምብ – ዮሐ 12፥1-8

1ፋሲካና የቂጣ በዓል ሊከበር ሁለት ቀን ሲቀረው፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ኢየሱስን የሚይዙበትና የሚገድሉበትን ዘዴ ይፈልጉ ነበር። 2ሆኖም፣ “ሕዝቡ ዐመፅ እንዳያነሣ በበዓሉ ሰሞን መሆን የለበትም” ይባባሉ ነበር።

3እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ ስምዖን ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ንጹሕ የናርዶስ ሽቱ የተሞላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፣ ቢልቃጡንም ሰብራ ሽቱውን በራሱ ላይ አፈሰሰችው።

4በዚያ ከነበሩት አንዳንዶቹ በድርጊቱ ተቈጥተው እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ሽቱው ለምን በከንቱ ይባክናል? 5ከሦስት መቶ ዲናር በላይ ተሸጦ፣ ገንዘቡን ለድኾች መስጠት ይቻል ነበር።” ሴትዮዋንም ነቀፏት።

6ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ተዉአት፣ ለምን ታስቸግሯታላችሁ? መልካም ነገር አድርጋልኛለች። 7ድኾች ምንጊዜም ከእናንተ ጋር ናቸው፤ በፈለጋችሁ ጊዜ ልትረዷቸው ትችላላችሁ፤ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤ 8እርሷ ማድረግ የምትችለውን ያህል አድርጋለች፤ ለመቃብሬ እንዲሆን ሰውነቴን አስቀድማ ቀብታለች። 9እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በሚሰበክበት በማንኛውም ስፍራ እርሷ ያደረገችው መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል።”

10ከዚህ በኋላ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ። 11እነርሱም ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፤ ገንዘብ ሊሰጡትም ቃል ገቡለት፤ ስለዚህ እርሱን አሳልፎ የሚሰጥበትን ምቹ ጊዜ ይጠባበቅ ነበር።

የጌታ እራት

14፥12-26 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥17-30ሉቃ 22፥7-23

14፥22-25 ተጓ ምብ – 1ቆሮ 11፥23-25

12የፋሲካ በግ በሚታረድበት በቂጣ በዓል የመጀመሪያው ቀን፣ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “የፋሲካ እራት የት እንድናዘጋጅልህ ትፈልጋለህ?” አሉት።

13እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ከተማ ሂዱ፤ እንስራ ውሃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ 14ወደሚገባበት ቤትም ተከተሉት፤ የቤቱንም ጌታ፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን ራት የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የትኛው ነው?’ ብሏል በሉት፤ 15እርሱም በሰገነቱ ላይ የተሰናዳና የተነጠፈ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ እዚያ አዘጋጁልን።”

16ደቀ መዛሙርቱም ወጥተው ወደ ከተማዪቱ ሄዱ፤ ማንኛውም ነገር ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካውንም አሰናዱ።

17በመሸም ጊዜ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር መጣ። 18በማእድ ላይ ሳሉም፣ “እውነት እላችኋለሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ፣ አብሮኝ የሚበላው እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል” አላቸው።

19እነርሱም ዐዘኑ፤ እያንዳንዳቸውም፣ “እኔ እሆንን?” ይሉት ጀመር።

20እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፣ ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ውስጥ የሚያጠልቀው ነው። 21የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጥ ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።”

22ሲበሉም እንጀራ አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸውና፣ “ዕንኩ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” አላቸው።

23ጽዋውንም አነሣ፤ አመስግኖም ሰጣቸው፤ ሁሉም ከዚያ ጠጡ።

24ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስስ የአዲስ14፥24 አንዳንድ ቅጆች “አዲስ” የሚለው ቃል የላቸውም። ኪዳን ደሜ ነው፤ 25እውነት እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት አዲሱን የወይን ፍሬ እስከምጠጣበት እስከዚያች ቀን ድረስ ዳግም ይህን አልጠጣም።”

26ከዚህ በኋላ መዝሙር ዘምረው ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጡ።

ጴጥሮስ እንደሚክደው ኢየሱስ አስቀድሞ ተናገረ

14፥27-31 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥31-35

27ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ፤

“ ‘እረኛውን እመታለሁ በጎቹም ይበተናሉ’

28ከተነሣሁ በኋላ ግን፣ ቀድሜአችሁ ወደ ገሊላ እሄዳለሁ።”

29ጴጥሮስም፣ “ሁሉም ቢሰናከሉ እንኳ እኔ አላደርገውም” አለ።

30ኢየሱስም፣ “እውነት እልሃለሁ፤ በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት14፥30 አንዳንድ የጥንት ቅጆች “ሁለት ጊዜ” የሚለው ሐረግ የላቸውም። ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።

31ጴጥሮስም፣ “ከአንተ ጋር ብሞት እንኳ ከቶ አልክድህም” በማለት ይበልጥ አጽንቶ ተናገረ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።

ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ጸለየ

14፥32-42 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥36-46ሉቃ 22፥40-46

32ከዚህ በኋላ ጌቴሴማኒ ወደሚባል ስፍራ ሄዱ፤ ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “እኔ ስጸልይ እናንተ እዚህ ቈዩ” አላቸው። 33ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስንም ይዞ ሄደ፤ እጅግ ያዝን ይጨነቅ ጀመር። 34ደግሞም፣ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ ዐዘነች፤ እዚሁ ሁኑና ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው።

35ጥቂት ዕልፍ ብሎም በምድር ላይ በመውደቅ ቢቻል ሰዓቱ ከእርሱ እንዲያልፍ ጸለየና፣ 36“አባ14፥36 በአራማይክ ቋንቋ አባት የሚጠራበት ነው።፤ አባት ሆይ፤ ሁሉ ነገር ይቻልሃልና ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ።

37ተመልሶም ሲመጣ ደቀ መዛሙርቱን ተኝተው አገኛቸው፤ ጴጥሮስንም እንዲህ አለው፣ “ስምዖን ሆይ፤ ተኝተሃልን? አንድ ሰዓት እንኳ ነቅተህ መጠበቅ አቃተህ? 38ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩም፤ መንፈስ ዝግጁ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው።”

39እንደ ገናም ሄዶ መጀመሪያ የጸለየውን ደግሞ ጸለየ። 40ዳግመኛም ሲመለስ ዐይናቸውን እንቅልፍ ከብዶት ተኝተው አገኛቸው፤ የሚመልሱለትንም አያውቁም ነበር።

41ሦስተኛ ጊዜም መጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “አሁንም እንደ ተኛችሁና እንዳረፋችሁ ናችሁ? ይበቃል! ሰዓቲቱ ደርሳለች፤ እነሆ፤ የሰው ልጅ ለኀጢአተኞች እጅ ዐልፎ ይሰጣል። 42ተነሡ፤ እንሂድ፤ አሳልፎ የሚሰጠኝ መጥቷል።”

ኢየሱስ ተያዘ

14፥43-50 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥47-56ሉቃ 22፥47-50ዮሐ 18፥3-11

43ወዲያው እየተናገረ ሳለ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፤ አብረውትም ሰይፍና ዱላ የያዙ፣ ከካህናት አለቆች፣ ከጸሓፍትና ከሽማግሌዎች የተላኩ ብዙ ሰዎች ነበሩ።

44አሳልፎ የሚሰጠውም፣ “እኔ የምስመው እርሱ ነውና ያዙት፤ ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት” በማለት አስቀድሞ ምልክት ሰጥቷቸው ነበር። 45እንደ ደረሰም ወዲያው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “መምህር ሆይ!” ብሎ ሳመው፤ 46ሰዎቹም ኢየሱስን ያዙት አሰሩትም። 47በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዱ ሰይፉን መዝዞ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ ጆሮ ቈረጠ።

48ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እንደ ወንበዴ በሰይፍና በቈመጥ ልትይዙኝ መጣችሁን? 49በየዕለቱም በቤተ መቅደስ እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ።” 50በዚህ ጊዜ ሁሉም ትተውት ሸሹ።

51ዕርቃኑን ለመሸፈን በፍታ ያገለደመ አንድ ወጣት ኢየሱስን ይከተል ነበር። ሰዎቹም ይህን ወጣት በያዙት ጊዜ፣ 52ግልድሙን ጥሎ ዕራቍቱን ሸሸ።

ኢየሱስ በሸንጎ ፊት

14፥53-65 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥57-68ዮሐ 18፥121319-24

14፥61-63 ተጓ ምብ – ሉቃ 22፥67-71

53ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። 54ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፣ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር።

55የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። 56ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። 57አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ 58“ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።” 59ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም።

60ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። 61ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም።

ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ14፥61 ወይም መሲሑ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው።

62ኢየሱስም፣ “አዎን ነኝ፤ የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ሲቀመጥ፣ በሰማይ ደመናም ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለ።

63ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና፣ እንዲህ አለ፤ “ሌላ ምን ምስክር ያስፈልገናል? 64ስድቡን ሰምታችኋል፤ ታዲያ ምን ይመስላችኋል?”

እነርሱም ሞት ይገባዋል በማለት በአንድ ቃል ፈረዱበት። 65በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ይተፉበት ጀመር፤ ዐይኑንም ሸፍነው በጡጫ እየመቱት፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር!” ይሉት ነበር። ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።

ጴጥሮስ ኢየሱስን አላውቀውም አለ

14፥66-72 ተጓ ምብ – ማቴ 26፥69-75ሉቃ 22፥56-62ዮሐ 18፥16-1825-27

66ጴጥሮስ በግቢው ውስጥ በታችኛው በኩል ሳለ፣ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፤ 67ጴጥሮስ እሳት ሲሞቅ አይታ ትኵር ብላ ተመለከተችውና፣ “አንተም ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ነበርህ” አለችው።

68እርሱ ግን፣ “የምትዪውን አላውቅም፤ አይገባኝምም” በማለት ካደ። ከዚያም ወደ መግቢያው በር ወጣ አለ፤ በዚህ ጊዜ ዶሮ ጮኸ።14፥68 አንዳድ ቅጆች “ዶሮ ጮኸ” የሚለው የላቸውም።

69ገረዲቱም ባየችው ጊዜ እዚያ ለቆሙት፣ “ይህ ሰው ከእነርሱ አንዱ ነው” ብላ እንደ ገና ተናገረች። 70እርሱ ግን አሁንም ካደ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በዚያ የቆሙት ሰዎች ጴጥሮስን፣ “የገሊላ ሰው እንደ መሆንህ መጠን፣ በርግጥ አንተ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አሉት።

71እርሱ ግን፣ “እናንተ የምትሉትን ሰው እኔ አላውቀውም” እያለ ይምል ይገዘት ጀመር።

72ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ14፥72 አንዳንድ የጥንት ቅጆች “ሁለተኛ” የሚለው ቃል የላቸውም። ጮኸ። ጴጥሮስም፣ “ዶሮ ሁለት ጊዜ14፥72 አንዳንድ የጥንት ቅጆች “ሁለት ጊዜ” የሚለው ሐረግ የላቸውም። ከመጮኹ በፊት ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው። ከዚያም ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።