መዝሙር 129 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 129:1-8

መዝሙር 129

በጽዮን ጠላቶች ላይ የቀረበ ጸሎት

መዝሙረ መዓርግ።

1እስራኤል እንዲህ ይበል፦

“ከልጅነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ አስጨነቁኝ፤

2በርግጥ ከልጅነቴ ጀምሮ ብዙ ጊዜ አስጨነቁኝ፤

ዳሩ ግን ድል አላደረጉኝም።

3ዐራሾች ጀርባዬን ዐረሱት፤

ትልማቸውንም አስረዘሙት።”

4እግዚአብሔር ግን ጻድቅ ነው፤

የክፉዎችን ገመድ በጣጥሶ ጣለው።

5ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ፣

ዐፍረው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።

6ገና ከመብቀሉ እንደሚደርቅ፣

በጣራ ላይ እንደ በቀለ ሣር ይሁኑ፤

7ደግሞም ለዐጫጅ እጁን፣

ለነዶ ሰብሳቢ ዕቅፉን እንደማይሞላ ይሁኑ።

8መንገድ ዐላፊዎችም፣

የእግዚአብሔር በረከት በእናንተ ላይ ይሁን፤

በእግዚአብሔር ስም እንባርካችኋለን” አይበሉ።