ምሳሌ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ምሳሌ 1:1-33

መግቢያ፤ የምሳሌዎቹ ዐላማና ጭብጥ

1የእስራኤል ንጉሥ፣ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ምሳሌዎች፤

2ጥበብንና ተግሣጽን ለመቀበል፤

ጥልቅ ሐሳብ የሚገልጡ ቃላትን ለማስተዋል፤

3ጽድቅን፣ ፍትሕንና ሚዛናዊ ብያኔን በማድረግ፣

የተገራ ጠቢብ ልቦናን ለማግኘት፤

4ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣

በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን ለመስጠት፤

5ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤

አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት፤

6ይህም የጠቢባንን ምሳሌዎችና ተምሳሌቶች፣

አባባሎችና ዕንቈቅልሾች ይረዱ ዘንድ ነው።

7እግዚአብሔርን መፍራት የዕውቀት መጀመሪያ ነው፤

ተላሎች1፥7 በመጽሐፈ ምሳሌና በብሉይ ኪዳን ሌሎች መጻሕፍት ውስጥ ተላላ የሚለው በተደጋጋሚ ተጽፏል፤ ይህም የሞራል ጕድለትን ያመለክታል። ግን ጥበብንና ተግሣጽን ይንቃሉ።

ጥበብን ገንዘብ ለማድረግ የተሰጠ ምክር

8ልጄ ሆይ፤ የአባትህን ምክር አድምጥ፤

የእናትህንም ትምህርት አትተው።

9ለራስህ ሞገስን የሚያጐናጽፍ አክሊል፣

ዐንገትህን የሚያስውብ ድሪ ይሆንልሃል።

10ልጄ ሆይ፤ ኀጢአተኞች ቢያባብሉህ፣

እሺ አትበላቸው፤

11“ከእኛ ጋር ናና፣ ደም ለማፍሰስ እናድባ፤

በደል በሌለበት ሰው ላይ እንሸምቅ፤

12እንደ መቃብር፣ ወደ ጕድጓድ1፥12 በዕብራይስጡ ሲኦል ይላል። እንደሚወርዱ፣

ከነሕይወታቸው እንዳሉ እንዋጣቸው፤

13ውድ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በየዐይነቱ እናገኛለን፤

ቤቶቻችንንም በዝርፊያ እንሞላለን፤

14ከእኛ ጋር ዕጣህን ጣል፤

የጋራ ቦርሳ ይኖረናል” ቢሉህ፣

15ልጄ ሆይ፤ አብረሃቸው አትሂድ፤

በሚሄዱበትም መንገድ እግርህን አታንሣ፤

16እግራቸው ወደ ኀጢአት ይቸኵላል፤

ደም ለማፍሰስም ፈጣኖች ናቸው።

17ወፎች ፊት እያዩ ወጥመድ መዘርጋት፣

ምንኛ ከንቱ ነው!

18እነዚህ ሰዎች የሚያደቡት በገዛ ደማቸው ላይ ነው፤

የሚሸምቁትም በራሳቸው ላይ ብቻ ነው።

19ያላግባብ ለጥቅም የሚሯሯጡ ሁሉ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤

የሕይወታቸው መጥፊያም ይኸው ነው።

ጥበብን ለሚያናንቁ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

20ጥበብ በጐዳና ላይ ጮኻ ትጣራለች፤

በየአደባባዩ ድምፅዋን ከፍ ታደርጋለች፤

21ዉካታ በበዛባቸው ጐዳናዎች ላይ1፥21 በዕብራይስጡና በሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች በቅጥሮች ጫፍ ላይ ይላሉ። ትጮኻለች፤

በከተማዪቱም መግቢያ በር ላይ እንዲህ ትላለች፤

22“እናንት ብስለት የሌላችሁ1፥22 በዕብራይስጡ ብስለት የሌለው የሚለው ቃል በዚህ መጽሐፍ በአጠቃላይ መልካም ምግባር የሌለውንና ክፋትን ለማድረግ ልቡ ያዘነበለ ሰውን ያመለክታል። ማስተዋል የሌለበት መንገዳችሁን እስከ መቼ ትወዱታላችሁ?

ፌዘኞች በፌዝ ደስ የሚሰኙት፣

ሞኞችስ ዕውቀትን የሚጠሉት እስከ መቼ ነው?

23ዘለፋዬን ብትሰሙኝ ኖሮ፣

ልቤን ባፈሰስሁላችሁ፣

ሐሳቤንም ባሳወቅኋችሁ ነበር።

24ነገር ግን በተጣራሁ ጊዜ እንቢ ስላላችሁኝ፣

እጄንም ስዘረጋ ማንም ግድ ስላልነበረው፣

25ምክሬን ሁሉ ስለ ናቃችሁ፣

ዘለፋዬንም ስላልተቀበላችሁ፣

26እኔ ደግሞ በመከራችሁ እሥቅባችኋለሁ፤

መዓት በሚወርድባችሁም ጊዜ አፌዝባችኋለሁ፤

27መዓት እንደ ማዕበል ሲያናውጣችሁ፣

መከራም እንደ ዐውሎ ነፋስ ሲጠራርጋችሁ፣

ሥቃይና ችግር ሲያጥለቀልቃችሁ አፌዝባችኋለሁ።

28“በዚያን ጊዜ ይጠሩኛል፤ እኔ ግን አልመልስላቸውም፤

አጥብቀው ይፈልጉኛል፤ ነገር ግን አያገኙኝም።

29ዕውቀትን ስለ ጠሉ፣

እግዚአብሔርንም መፍራት ስላልመረጡ፣

30ምክሬን ለመቀበል ስላልፈለጉ፣

ዘለፋዬን ስለ ናቁ፣

31የመንገዳቸውን ፍሬ ይበላሉ፤

የዕቅዳቸውንም ውጤት ይጠግባሉ።

32ብስለት የሌላቸውን ስድነታቸው ይገድላቸዋል፤

ተላሎችንም ቸልተኝነታቸው ያጠፋቸዋል፤

33የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤

ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።”