1 ነገሥት 16 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 16:1-34

1ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል በባኦስ ላይ እንዲህ ሲል ወደ አናኒ ልጅ ወደ ኢዩ መጣ፤ 2“ከትቢያ አንሥቼ፣ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግሁህ፤ አንተ ግን በኢዮርብዓም መንገድ ሄድህ፤ ሕዝቤ እስራኤል ኀጢአት እንዲሠራ፣ በኀጢአቱም ለቍጣ እንዲያነሣሣኝ አሳሳትኸው። 3ስለዚህ ባኦስንና ቤቱን ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ ቤትህንም እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት አደርገዋለሁ። 4በከተማዪቱ ውስጥ የሚሞቱትን የባኦስን ወገኖች ሁሉ ውሾች ይበሏቸዋል፤ በገጠር የሚሞቱትንም ሁሉ የሰማይ አሞሮች ይቀራመቷቸዋል።”

5በባኦስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ ሌላው ያደረገው ሥራው በሙሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 6ባኦስ፣ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በቴርሳም ተቀበረ። ልጁም ኤላ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

7ከዚህም በቀር የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ ኢዩ አማካይነት በባኦስና በቤቱ ላይ የመጣበት ምክንያት፣ በእጁ ሥራ ያስቈጣው ዘንድ እንደ ኢዮርብዓም ቤት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራን ሁሉ በማድረጉና ኢዮርብዓምን በማጥፋቱም ጭምር ነው።

የእስራኤል ንጉሥ ኤላ

8የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ስድስተኛው ዓመት የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በቴርሳ ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ።

9ከሹማምቱ አንዱና የግማሽ ሠረገሎቹ አዛዥ የሆነው ዘምሪ ዐምፆ ተነሣበት፤ በዚያን ጊዜ ኤላ በቴርሳ ከተማ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ በሆነው በአርጻ ቤት ጠጥቶ ሰክሮ ነበር፤ 10ዘምሪም ገብቶ ኤላን ገደለው፤ እርሱም በኤላ እግር ተተክቶ፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ነገሠ።

11ዘምሪ ወዲያው እንደ ነገሠና በዙፋን እንደ ተቀመጠ፣ የባኦስን ቤተ ሰብ በሙሉ ገደለ፤ የሥጋ ዘመድም ሆነ ወዳጅ አንድም ወንድ አላስቀረም። 12በዚህ ሁኔታም በነቢዩ በኢዩ አማካይነት በባኦስ ላይ በተነገረው በእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የባኦስን ቤተ ሰብ ሁሉ ፈጀ።

13ይህም የሆነው ባኦስና ልጁ ኤላ፣ በማይረቡ ጣዖቶቻቸው ምክንያት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ በሠሩት ኀጢአት ሁሉና፣ እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ነበር።

14ሌላው ኤላ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

የእስራኤል ንጉሥ ዘምሪ

15የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሃያ ሰባተኛው ዓመት ዘምሪ በቴርሳ ሆኖ ሰባት ቀን ብቻ ገዛ። በዚህ ጊዜ ሰራዊቱ የፍልስጥኤማውያን ከተማ የሆነችውን ገባቶንን ከብቦ ሰፍሮ ነበር። 16በዚያም ሰፈር የነበሩ እስራኤላውያን ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን እንደ ሰሙ፣ የሰራዊቱን አዛዥ ዖምሪን በዚያኑ ዕለት እዚያው ሰፈር ውስጥ በእስራኤል ላይ ማንገሣቸውን ዐወጁ። 17ከዚያም ዖምሪና አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ ከገባቶን ወደ ላይ ወጥተው ቴርሳን ከበቡ። 18ዘምሪ ከተማዪቱ መያዟን ሲያይ፣ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ግንብ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበትና በዚሁ ሞተ። 19ይህ የሆነውም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ በመሥራትና በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድ፣ እንዲሁም ራሱ በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ ባደረገው ኀጢአት ምክንያት ነው።

20ሌላው ዘምሪ በዘመኑ የፈጸመው ድርጊትና ያካሄደውም ዐመፅ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

የእስራኤል ነጉሥ ዖምሪ

21ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ከሁለት ተከፈለ፣ ይህም ግማሹ የጎናትን ልጅ ታምኒን ለማንገሥ ሲሆን፣ የቀረው ደግሞ ዖምሪን በመደገፍ ነበር። 22ሆኖም የዖምሪ ተከታዮች ከጎናት ልጅ ከታምኒ ተከታዮች ይልቅ በረቱ፤ ስለዚህ ታምኒ ሞተ፤ ዖምሪም ነገሠ።

23የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት፣ ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ገዛ፤ ከዚህም ውስጥ ስድስቱን ዓመት የገዛው በቴርሳ ሆኖ ነው። 24እርሱም የሰማርያን ኰረብታ በሁለት መክሊት16፥24 70 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ጥሬ ብር ከሳምር ላይ ገዝቶ ከተማ ሠራባት፤ ስሟንም በቀድሞው የተራራዋ ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራት።

25ይሁን እንጂ ዖምሪ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩትም ይልቅ የበለጠ ኀጢአት ሠራ። 26እርሱም እስራኤል በማይረቡ ጣዖቶቻቸው፣ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ እንዲያነሣሡት ባደረገው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሁሉና እርሱም ኀጢአት ሠርቶ እስራኤልም እንዲሠሩ ባደረገው ኀጢአት ተመላለሰ።

27ሌላው ዖምሪ በዘመኑ የፈጸመው፣ ያደረገውና ያከናወነው ሁሉ በእስራኤል የነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 28ዖምሪ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ተቀበረ፤ ልጁም አክዓብ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

አክዓብ የእስራኤል ንጉሥ ሆነ

29የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት፣ የዖምሪ ልጅ አክዓብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፣ በሰማርያም ሆኖ እስራኤልን ሃያ ሁለት ዓመት ገዛ። 30የዖምሪ ልጅ አክዓብ ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩት ሁሉ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 31የናባጥን ልጅ የኢዮርብዓምን ኀጢአት እንደ ቀላል ነገር ከመቍጠሩም በላይ የሲዶናውያንን ንጉሥ የኤትበኣልን ልጅ ኤልዛቤልን አገባ፤ ሄዶም በኣልን አመለከ፤ ሰገደለትም። 32ሰማርያ ላይ በሠራውም የበኣል ቤተ ጣዖት ለበኣል መሠዊያ አቆመለት። 33ደግሞም አክዓብ የአሼራን ምስል ዐምድ በማቆም ከእርሱ በፊት ከነበሩት የእስራኤል ነገሥታት ይልቅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ የሚያነሣሣ ድርጊት ፈጸመ።

34የቤቴል ሰው አኪኤል፣ በአክዓብ ዘመን ኢያሪኮን መልሶ ሠራት። እግዚአብሔር በነዌ ልጅ በኢያሱ አማካይነት የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ መሠረቷን ሲያኖር በኵር ልጁ አቢሮን ሞተ፤ የቅጽር በሮቿንም በሚሠራበት ጊዜ የመጨረሻው ልጁ ሠጉብ ሞተ።