2 ሳሙኤል 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ሳሙኤል 1:1-27

ዳዊት የሳኦልን ሞት ሰማ

1፥4-12 ተጓ ምብ – 1ሳሙ 31፥1-131ዜና 10፥1-12

1ሳኦል ከሞተ በኋላ፣ ዳዊት አማሌቃውያንን ድል አድርጎ በመመለስ፣ በጺቅላግ ሁለት ቀን ቈየ። 2በሦስተኛውም ቀን የተቀደደ ልብስ የለበሰ፣ በራሱም ላይ ትቢያ የነሰነሰ አንድ ሰው ከሳኦል ሰፈር መጣ። ወደ ዳዊት እንደ ደረሰም፣ ወደ መሬት ለጥ ብሎ በአክብሮት እጅ ነሣ።

3ዳዊትም፣ “ከወዴት መጣህ?” ሲል ጠየቀው።

እርሱም፣ “ከእስራኤላውያን ሰፈር ሸሽቼ መምጣቴ ነው” በማለት መለሰለት።

4ዳዊትም፣ “ምን ነገር ተፈጠረ?” ሲል ጠየቀው።

እርሱም፣ “ሰዎቹ ከጦርነቱ ሸሽተዋል፤ ብዙዎቹ ወድቀዋል፤ ሞተዋል፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ሞተዋል” አለ።

5ከዚያም ዳዊት ወሬውን የነገረውን ወጣት፣ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን መሞታቸውን እንዴት ዐወቅህ?” ሲል ጠየቀው።

6ወሬ ነጋሪው ወጣትም እንዲህ አለ፤ “ድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ ወጥቼ ነበር፤ እዚያም ሳኦል ጦሩን ተደግፎ ሳለ፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ተከታትለው ደረሱበት። 7ወደ ኋላውም ዞር ሲል እኔን ስላየ ጠራኝ፤ እኔም፣ ‘ምን ልታዘዝ’ አልሁ።

8“እርሱም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ሲል ጠየቀኝ፤

“እኔም ‘አማሌቃዊ ነኝ’ ብዬ መለስሁለት።

9“ከዚያም፣ ‘እኔ በሞት ጣር ውስጥ እገኛለሁ፤ ነፍሴ ግን አልወጣችም፤ እባክህ በላዬ ቆመህ ግደለኝ’ አለኝ።

10“መቼም ከወደቀ በኋላ እንደማይተርፍ ስላወቅሁ፣ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱ ላይ የነበረውን ዘውድና የክንዱን አንባር ወስጄ እነሆ፤ ለጌታዬ አምጥቻለሁ።”

11ከዚያም ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። 12ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፣ ለእግዚአብሔር ሰራዊትና ለእስራኤል ቤት ዐዘኑ፤ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ፤ የወደቁት በሰይፍ ነበርና።

13ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ወጣት፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” ብሎ ጠየቀው።

እርሱም፣ “እኔ የአንድ መጻተኛ አማሌቃዊ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ።

14ዳዊትም፣ “ታዲያ እግዚአብሔር የቀባውን ለማጥፋት እጅህን ስታነሣ እንዴት አልፈራህም?” ሲል ጠየቀው።

15ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፣ “በል ቅረብና ውደቅበት” አለው። እርሱም መታው፤ ሞተም። 16ዳዊትም፣ “ ‘እግዚአብሔር የቀባውን ገድያለሁ’ ስትል የገዛ አፍህ መስክሮብሃልና፣ ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።

ዳዊት ለሳኦልና ለዮናታን የተቀኘው የሐዘን እንጕርጕሮ

17ዳዊትም በሳኦልና በልጁ በዮናታን ሞት ምክንያት ይህን የሐዘን እንጕርጕሮ እየተቀኘ አለቀሰ፤ 18እንዲሁም የቀስት እንጕርጕሮ የተባለውን ለይሁዳ ሕዝብ እንዲያስተምሩ አዘዘ፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፏል።

19“እስራኤል ሆይ፤ ክብርህ በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል፤

ኀያላኑ እንዴት እንደዚህ ይውደቁ!

20“ይህን በጌት አትናገሩ፤

በአስቀሎናም መንገዶች አታውጁት፤

የፍልስጥኤም ቈነጃጅት አይደሰቱ፤

ያልተገረዙት ሴቶች ልጆች እልል አይበሉ።

21“እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፤

ጠል አያረስርሳችሁ፤

ዝናብም አይውረድባችሁ፤

የቍርባን እህል የሚያበቅሉም ዕርሻዎች አይኑራቸው፤

በዚያ የኀያሉ ሰው ጋሻ ረክሷልና፤ የሳኦል ጋሻ ከእንግዲህ በዘይት አይወለወልም።

22“ከሞቱት ሰዎች ደም፣

ከኀያላኑም ሥብ፣

የዮናታን ቀስት ተመልሳ አልመጣችም፤

የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰችም።

23ሳኦልና ዮናታን በሕይወት እያሉ፣

የሚዋደዱና የሚስማሙ ነበሩ፤

ሲሞቱም አልተለያዩም፤

ከንስርም ይልቅ ፈጣኖች፣

ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።

24“እናንት የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፤

ሐምራዊ ቀሚስና ቀጭን ፈትል ላለበሳችሁ፣

ልብሶቻችሁንም በወርቀ ዘቦ ላስጌጠላችሁ፣

ለሳኦል አልቅሱለት።

25“ኀያላን እንዴት እንዲህ በጦርነት ወደቁ!

ዮናታን በኰረብቶችህ ላይ ተወግቶ ሞቷል።

26ወንድሜ ዮናታን ሆይ፤ እኔ ስለ አንተ ዐዘንሁ፤

አንተ ለእኔ እጅግ ውድ ነበርህ፤

ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ፤

ከሴት ፍቅርም ይልቅ ግሩም ነበር።

27“ኀያላኑ እንዴት ወደቁ!

የጦር መሣሪያዎቹስ እንዴት ከንቱ ይሁኑ!”