1 ነገሥት 10 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ነገሥት 10:1-29

ንግሥተ ሳባ ሰሎሞንን እንደ ጐበኘች

10፥1-13 ተጓ ምብ – 2ዜና 9፥1-12

1ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ዝና እና ከእግዚአብሔር ስም ጋር ያለውን ግንኙነት በሰማች ጊዜ፣ አስቸጋሪ በሆኑ ጥያቄዎች ልትፈትነው መጣች። 2ታላቅ አጀብ አስከትላ ሽቶ፣ እጅግ ብዙ ወርቅና የከበሩ ዕንቈች በግመል አስጭና ኢየሩሳሌም ከደረሰች በኋላ፣ ወደ ሰሎሞን ገብታ በልቧ ያለውን ጥያቄ ሁሉ አቀረበችለት። 3ሰሎሞንም የጠየቀችውን ሁሉ መለሰላት፤ ንጉሡ አቅቶት የቀረ አንዳች ጥያቄ አልነበረም። 4ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ጥበብ ሁሉ፣ የሠራውንም ቤተ መንግሥት ስትመለከት 5እንዲሁም በገበታው ላይ የሚቀርበውን መብል፣ የሹማምቱን አቀማመጥ፣ አሳላፊዎቹን ከነደንብ ልብሳቸው፣ ጠጅ አሳላፊዎቹን፣ ደግሞም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያቀረበውን የሚቃጠል መሥዋዕት10፥5 ወይም ወደ ላይ የሚወጣባቸው ደረጃዎች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ስታይ እጅግ ተደነቀች።

6ንጉሡንም እንዲህ አለችው፤ “ስላከናወንኸው ሥራና ስለ ጥበብህ በአገሬ ሳለሁ የሰማሁት ትክክል ነው፤ 7ይሁን እንጂ፣ ራሴ መጥቼ እነዚህን ነገሮች በዐይኔ እስካይ ድረስ አላመንሁም ነበር፤ በርግጥ ግማሹን እንኳ አልነገሩኝም፤ ጥበብህና ብልጽግናህ ከሰማሁት በላይ ነው። 8ሰዎችህ እንዴት ያሉ ዕድለኞች ናቸው! ሁልጊዜ በፊትህ ቆመው ጥበብህን የሚሰሙ ሹማምትህስ እንዴት የታደሉ ናቸው! 9በአንተ ደስ ተሰኝቶ በእስራኤል ዙፋን ላይ ያስቀመጠህ እግዚአብሔር አምላክህ የተመሰገነ ይሁን፤ እግዚአብሔር በዘላለም ፍቅሩም እስራኤልን ከመውደዱ የተነሣ፣ ፍትሕና ጽድቅ እንዲሰፍን አንተን ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።”

10ለንጉሡም መቶ ሃያ መክሊት10፥10 4 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። ወርቅ፣ እጅግ ብዙ ሽቶና የከበረ ድንጋይ ሰጠችው፤ ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰሎሞን ያበረከተችለትን ያን ያህል ብዛት ያለው ሽቶ ከዚያ በኋላ ከቶ አልመጣም።

11ከኦፊር ወርቅ ያመጡት የኪራም መርከቦች፣ እጅግ ብዙ የሰንደል ዕንጨትና10፥11 በዚህና በ12 ላይ፣ የአልጉም ዕንጨት ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። የከበሩ ዕንቈችም አመጡ። 12ንጉሡም የሰንደሉን ዕንጨት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና ለቤተ መንግሥቱ መደገፊያ፣ ለበገናና ለመሰንቆ መሥሪያ አዋለው። ይህን ያህል ብዛት ያለው የሰንደል ዕንጨት እስከ ዛሬ ድረስ ከቶ አልመጣም፤ አልታየምም።

13ንጉሥ ሰሎሞንም ለንግሥተ ሳባ ከቤተ መንግሥቱ በልግስና ከሚሰጣት ሌላ፣ የፈለገችውንና የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣት፤ ከዚያም ከአጃቢዎቿ ጋር ወደ አገሯ ተመለሰች።

የሰሎሞን ብልጽግናና ክብር

10፥14-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 1፥14-179፥13-28

14ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበር።10፥14 23 ሜትሪክ ቶን ያህል ነው። 15ይህም ከንግድና ከሌላ ገቢ ላይ የሚከፈለውን ቀረጥ፣ የዐረብ ነገሥታት ሁሉ የሚያገቡትንና አገረ ገዦች የሚሰበስቡትን ግብር ሳይጨምር ነው።

16ንጉሥ ሰሎሞን ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሁለት መቶ ታላላቅ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ሦስት መቶ ሰቅል10፥16 3.5 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ወርቅ ነበር። 17እንዲሁም ከተጠፈጠፈ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻ አሠራ፤ በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ደግሞ ሦስት ምናን10፥17 1.7 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ወርቅ ነው። ንጉሡም እነዚህን የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት አኖረ።

18ከዚያም ንጉሡ ከዝሆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን አሠርቶ በንጹሕ ወርቅ አስለበጠው። 19ዙፋኑ ባለ ስድስት ደረጃ ነው፤ በስተ ኋላውም ዐናቱ ላይ ክብ ቅርጽ ሲኖረው፣ ግራና ቀኙ ባለመደገፊያ ነው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። 20በስድስቱም ደረጃ ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ስድስት ስድስት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለም ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ከቶ ተሠርቶ አያውቅም። 21ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣበት ዋንጫ ሁሉ የወርቅ ሲሆን፣ የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበረው ዕቃ በሙሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ነበር፤ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ብር ይህን ያህል ዋጋ ስላልነበረው፣ ከብር የተሠራ ዕቃ ፈጽሞ አልነበረም። 22ንጉሡ ከኪራም መርከቦች ጋር አብረው በባሕር ላይ የሚጓዙ የተርሴስ የንግድ መርከቦች10፥22 ዕብራይስጡ የተርሴስ መርከቦች ይላል። ነበሩት። እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች ያመጡ ነበር።

23ንጉሥ ሰሎሞንም በሀብትና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። 24ዓለሙ ሁሉ እግዚአብሔር በሰሎሞን ልብ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ወደ እርሱ መምጣት ይፈልግ ነበር። 25በየዓመቱም የሚመጣው ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ሽቶ፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር።

26ሰሎሞን ሠረገሎችና10፥26 ወይም ሠረገለኞች ተብሎ መተርጐም ይችላል። ፈረሶች ሰበሰበ፤ አንድ ሺሕ አራት መቶ ሠረገሎችና ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት። እነዚህንም ሁሉ ሠረገሎች በሚያኖርበት ከተሞችና ራሱ በሚኖርበት በኢየሩሳሌም እንዲሆኑ አደረገ። 27ንጉሡም ብሩን በየቦታው እንደሚገኝ ድንጋይ አደረገ፤ የዝግባውም ዕንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። 28የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብፅና10፥28 በዚህና በ29 ላይ ምናልባት በቂልቂያ የምትገኘዋ ሙዘር ልትሆን ትችላለች። ከቀዌ10፥28 ምናልባትም ኪልቂያ ልትሆን ትችላለች። ሲሆን፣ እነዚህንም ከቀዌ ገዝተው ያመጧቸው የቤተ መንግሥቱ ንግድ ሰዎች ነበሩ። 29አንዱን ሠረገላ ከግብፅ የሚያመጡት በስድስት መቶ ሰቅል10፥29 7 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ሲሆን፣ ፈረሱን ደግሞ በመቶ አምሳ ሰቅል10፥29 1.7 ኪሎ ግራም ያህል ነው። ብር ያመጡ ነበር፤ ለኬጢያውያንና ለሶርያ ነገሥታትም አምጥተው ይሸጡላቸው ነበር።