ዘዳግም 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 12:1-32

ብቸኛው የማምለኪያ ስፍራ

1የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ)፣ እንድትወርሷት በሰጣችሁ ምድር ላይ በምትኖሩበት ጊዜ ሁሉ፣ በጥንቃቄ ልትከተሏቸው የሚገባችሁ ሥርዐቶችና ሕግጋት እነዚህ ናቸው። 2ከምድራቸው የምታስለቅቋቸው አሕዛብ በረጃጅም ተራሮች፣ በኰረብቶችና በእያንዳንዱ ዛፍ ሥር አማልክታቸውን የሚያመልኩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ። 3መሠዊያዎቻቸውን አፍርሱ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ሰባብሩ፤ የአሼራ ምስል ዐምዶቻቸውን በእሳት አቃጥሉ፤ የአማልክታቸውን ጣዖቶች ቈራርጣችሁ ጣሉ፤ ስማቸውንም ከእነዚያ ስፍራዎች ላይ አጥፉ።

4በእነርሱ መንገድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አታምልኩ። 5ዳሩ ግን አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆነው፣ በነገዶቻችሁ መካከል የሚመርጠውን ስፍራ እሹ፤ ወደዚያም ስፍራ ሂዱ። 6ወደዚያም የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራታችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ ስእለቶቻችሁንና የፈቃዳችሁን ስጦታዎች፣ የቀንድ ከብት መንጋችሁን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችሁን በኵራት አምጡ። 7በዚያም በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበላላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ያህዌ ኤሎሂም) እናንተን በባረከበት፣ በምታደርጉት ሁሉ አንተና ቤተ ሰዎችህ ሐሤት ታደርጋላችሁ።

8ዛሬ እንደምናደርገው ሁሉ፣ እያንዳንዱ የሚመስለውን እንዳደረገ አታድርጉ፤ 9ምክንያቱም ማረፊያ ወደ ሆነውና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚሰጣችሁ ርስት ገና አልደረሳችሁም። 10ይሁን እንጂ ዮርዳኖስን ስትሻገሩና አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ርስት አድርጎ በሚሰጣችሁ ምድር ስትቀመጡ፣ ያለ ሥጋት እንድትኖሩ በዙሪያችሁ ካሉት ጠላቶቻችሁ ሁሉ ያሳርፋችኋል። 11ከዚያም አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን ወደሚመርጠው ስፍራ፣ እኔ የማዝዛችሁን ሁሉ፦ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶቻችሁንና ሌሎች መሥዋዕቶቻችሁን፣ ዐሥራቶቻችሁንና የእጃችሁን ስጦታ፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተሳላችኋቸውን ምርጥ ነገሮች ሁሉ ወደዚያ ታመጣላችሁ። 12እዚያም እናንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻችሁ፣ እንዲሁም የራሳቸው ድርሻ ወይም ርስት የሌላቸው በየከተሞቻችሁ የሚኖሩት ሌዋውያን በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት አድርጉ። 13የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን በፈለግኸው ስፍራ ሁሉ እንዳታቀርብ ተጠንቀቅ። 14ከነገዶችህ መካከል በአንዱ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብቻ የሚቃጠሉ መሥዋዕቶችህን አቅርብ፤ እዚያም እኔ የማዝዝህን ሁሉ ጠብቅ።

15ሆኖም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ መጠን፣ በየትኛውም ከተማህ፣ እንስሳትህን ሚዳቋም ሆነ ድኵላ ዐርደህ የምትፈልገውን ያህል ሥጋ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነም ሆነ ያልሆነ ሰው ከዚሁ ሥጋ ሊበላ ይችላል። 16ደሙን ግን እንደ ውሃ መሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 17የእህልህን፣ የወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ ወይም የቀንድ ከብት፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት፣ ወይም ለመስጠት የተሳልኸውን ወይም የፈቃድህን ስጦታ፣ ወይም የእጅህን ስጦታ፣ በከተሞችህ ውስጥ መብላት የለብህም። 18አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ የሚኖር ሌዋዊም፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ትበሉታላችሁ፤ እጅህም በነካው ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይልሃል። 19በምድርም ላይ በምትኖርበት ጊዜ ሁሉ ሌዋዊውን ቸል እንዳትለው ተጠንቀቅ።

20አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ግዛትህን ሲያሰፋልህ፣ ሥጋ አምሮህ፣ “ሥጋ መብላት እፈልጋለሁ” በምትልበት ጊዜ፣ ያሰኘህን ያህል ሥጋ መብላት ትችላለህ። 21ስሙን ለማኖር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የመረጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ የራቀ ከሆነ፣ ባዘዝሁህ መሠረት ከቀንድ ከብትህ፣ ከበግና ከፍየል መንጋህ እንስሳት ማረድ ትችላለህ፤ በከተሞችህ ውስጥ የምትፈልገውን ያህል መብላት ትችላለህ፤ 22ሚዳቋ ወይም ድኵላ እንደሚበላ አድርገህ ብላ፤ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆኑትና ያልሆኑት ሊበሉ ይችላሉ። 23ደሙን ግን እንዳትበላ ተጠንቀቅ፤ ደም ሕይወት ስለሆነ፣ ሥጋን ከነሕይወቱ አትብላ። 24ደሙን እንደ ውሃ በመሬት ላይ አፍስሰው እንጂ አትብላው። 25በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላቸው አትብላው።

26ነገር ግን የተቀደሱ ነገሮችህን ለመስጠት የተሳልሃቸውን ሁሉ ይዘህ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። 27የሚቃጠል መሥዋዕትህን፣ ሥጋውንም ደሙንም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ላይ አቅርብ። የመሥዋዕትህ ደም በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሠዊያ ላይ ይፍሰስ፤ ሥጋውን ግን መብላት ትችላለህ። 28በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር ስለምታደርግ፣ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ ለዘላለም መልካም እንዲሆንላችሁ፣ እኔ የምሰጥህን እነዚህን ደንቦች ሁሉ በጥንቃቄ ፈጽማቸው።

29የምትወርሯቸውንና የምታስለቅቋቸውን አሕዛብ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከፊታችሁ ያስወግዳቸዋል፤ ባስወጣችኋቸውና በምድራቸው በተቀመጣችሁ ጊዜ ግን፣ 30ከፊትህ ከጠፉ በኋላ፣ “እነዚህ ሕዝቦች አማልክታቸውን የሚያመልኩት እንዴት ነው? እኔም እንደ እነርሱ አደርጋለሁ” ብለህ በመጠየቅ እንዳትጠመድ ተጠንቀቅ። 31አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በእነርሱ መንገድ ፈጽሞ አታምልክ፤ ምክንያቱም አማልክታቸውን ሲያመልኩ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚጸየፈውን ሁሉንም ዐይነት ነገር ያደርጋሉና፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን እንኳ ለአማልክታቸው መሥዋዕት አድርገው ያቃጥላሉ።

32እኔ ያዘዝሁህን ሁሉ ጠብቅ፤ አትጨምርበት፤ አትቀንስለትም።