ዘዳግም 11 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 11:1-32

እግዚአብሔርን ውደድ፤ ታዘዘውም

1እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ውደድ፤ ግዴታውን፣ ሥርዐቱን፣ ሕጉንና ትእዛዙን ሁልጊዜ ጠብቅ። 2የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፣ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደ ሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤ 3በግብፅ መካከል፣ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፣ 4በግብፃውያን ሰራዊት፣ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፣ እናንተን ባሳደዷችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር11፥4 ዕብራይስጡ፣ ያም ሳውፍ ይለዋል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው። ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና እግዚአብሔር (ያህዌ) ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤ 5ከምድረ በዳው አንሥቶ እዚህ እስከምትደርሱ ድረስ፣ ለእናንተ ያደረገላችሁን ያዩት ልጆቻችሁ አልነበሩም፤ 6የሮቤል ልጅ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንና አቤሮንን ከነቤተ ሰቦቻቸው፣ ከነድንኳናቸውና ከነእንስሳታቸው በመላው እስራኤል መካከል ምድር እንዴት አፏን ከፍታ እንደ ዋጠቻቸው እነርሱ አላዩም። 7የእናንተ ዐይኖች ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።

8ስለዚህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤ 9ለአባቶቻቸውና ለዘሮቻቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) ሊሰጣቸው በማለላቸው፣ በዚያች ማርና ወተት በምታፈስሰው ምድር ረዥም ዕድሜ ትኖሩ ዘንድ፣ 10የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም። 11ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት። 12ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ዐይን ምንጊዜም የማይለያት ናት።

13ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፣ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ብትወዱና በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል በታማኝነት ብትጠብቁ፣ 14እህልህን፣ ወይንህንና ዘይትህን እንድትሰበስብ የበልጉንና የክረምቱን ዝናብ በምድርህ ላይ በየወቅቱ አዘንባለሁ። 15በሜዳ ላይ ለከብቶችህ ሣር እሰጣለሁ፤ አንተም ትበላለህ፤ ትጠግባለህም።

16ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ተታልላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም። 17ከዚያም የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ እርሱም ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ። 18እነዚህን ቃሎቼን፣ በልባችሁና በአእምሯችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፣ በግምባራችሁም ላይ ይሁኑ። 19ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ ቤት ስትቀመጥ፣ መንገድ ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣ ስለ እነዚሁ አጫውታቸው። 20በቤትህ መቃኖችና በግቢህ በሮች ላይ ጻፋቸው፤ 21ይህን ካደረጋችሁ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል።

22አምላካችሁን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትወዱ ዘንድ፣ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከእርሱም ጋር ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣ 23እግዚአብሔር (ያህዌ) እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፣ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ። 24በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተ ምዕራብ እስካለው ባሕር11፥24 የሜዲትራንያን ባሕር ነው። ይደርሳል። 25ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።

26እነሆ፤ ዛሬ በረከትንና መርገምን በፊታችሁ አኖራለሁ፤ 27በረከቱ ዛሬ የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች ስትፈጽሙ ሲሆን፣ 28መርገሙ ደግሞ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዞች የማትፈጽሙ፣ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ለመከተል እኔ ከማዝዛችሁ መንገድ የምትወጡ ከሆነ ነው። 29ልትወርሳት ወደምትሄድባት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፣ መርገሙን ደግሞ በጌባል ተራራ ላይ ታሰማለህ። 30እነዚህ ተራሮች የሚገኙት ከዮርዳኖስ ማዶ11፥30 ወይም፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ። ፀሓይ በምትጠልቅበት አቅጣጫ ካለው መንገድ በስተ ምዕራብ በዓረባ በሚኖሩ የከነዓናውያን ምድር ውስጥ ከጌልገላ ፊት ለፊት፣ በሞሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ አይደለምን? 31አምላካችሁ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጣችሁ ምድር ትገቡባትና ትወርሷት ዘንድ ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ስለሆነ፣ ምድሪቱን ወርሳችሁ በምትኖሩባት ጊዜ፣ 32ዛሬ በፊታችሁ እኔ ያስቀመጥኋቸውን ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ ለመፈጸም ተጠንቀቁ።