ዘካርያስ 7 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘካርያስ 7:1-14

ፍትሕና ምሕረት የተወደደ ነው

1ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ካሴሉ በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ በአራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 2የቤቴል ሰዎች እግዚአብሔርን ለመለመን ሳራሳርንና ሬጌሜሌክን አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች ጋር ላኩ፤ 3እነርሱም የእግዚአብሔር ጸባኦት ቤት ካህናትና ነቢያት፣ “ብዙ ዓመት እንዳደረግሁት፣ በአምስተኛው ወር ማዘንና መጾም ይገባኛልን?” ብለው ጠየቁ።

4ከዚያም የእግዚአብሔር ጸባኦት ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 5“የምድሩን ሕዝብ ሁሉና ካህናቱን እንዲህ በላቸው፤ ‘ባለፉት ሰባ ዓመታት በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር የጾማችሁትና ያዘናችሁት በርግጥ ለእኔ ነበርን? 6ትበሉና ትጠጡ የነበረውስ ለራሳችሁ አይደለምን? 7ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች በሰላምና በብልጽግና ላይ ሳሉ፣ የደቡብና የምዕራብ ኰረብቶች ግርጌ የሰው መኖሪያም በነበሩበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር በቀደሙት ነቢያት የተናገረው ቃል ይህ አልነበረምን?’ ”

8የእግዚአብሔር ቃል እንደ ገና ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘እውነተኛ ፍትሕ አስፍኑ፣ እርስ በርሳችሁ ምሕረትና ርኅራኄን አድርጉ፤ 10መበለቲቱን ወይም ድኻ ዐደጉን፣ መጻተኛውን ወይም ድኻውን አታስጨንቁ፤ በልባችሁም አንዳችሁ በአንዳችሁ ላይ ክፉ አታስቡ።’

11“እነርሱ ግን መስማት አልፈለጉም፤ በእልኸኝነት ጀርባቸውን አዞሩ፤ ጆሯቸውንም ደፈኑ። 12ልባቸውን እንደ ባልጩት አጠነከሩ፤ እግዚአብሔር ጸባኦት በቀደሙት ነቢያት በኩል በመንፈሱ የላከውን ቃል ወይም ሕግ አልሰሙም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እጅግ ተቈጣ።

13“ ‘ስጠራቸው አልሰሙም፤ ስለዚህ ሲጠሩኝ አልሰማም’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። 14‘በማያውቋቸው በባዕዳን አሕዛብ መካከል በዐውሎ ነፋስ በተንኋቸው፤ ከእነርሱ በኋላ ማንም እስከማይመጣባትና እስከማይሄድባት ድረስ ምድሪቱ ባድማ ሆነች፤ መልካሚቱን ምድር ባድማ ያደረጓት በዚህ ሁኔታ ነው።’ ”