ኤርምያስ 9 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኤርምያስ 9:1-26

1ስለ ታረዱት ወገኖቼ፣

ቀንና ሌሊት አለቅስ ዘንድ፣

ምነው፣ ራሴ የውሃ ምንጭ በሆነ!

ምነው ዐይኖቼ የእንባ መጕረፊያ በሆኑልኝ!

2ሕዝቤን ትቼ፣ ርቄ እንድሄድ፣

በምድረ በዳ የእንግዶች ማደሪያ ማን በሰጠኝ!

ሁሉም አመንዝሮች፣

የአታላዮች መንጋ ሆነዋላ!

3“ሐሰትን ለመናገር፣

ምላሳቸውን እንደ ቀስት ገተሩ፤

በእውነት ሳይሆን፣

በሐሰት በምድሪቱ ገነኑ፤

ከክፋት ወደ ክፋት ሄዱ፤

እኔንም አላወቁኝም፤”

ይላል እግዚአብሔር

4“እያንዳንዱ ወንድም አታላይ፣9፥4 ወይም አታላይ ያዕቆብ

ባልንጀራም ሁሉ ሐሜተኛ ስለሆነ፣

ወንድም ከወንድሙ ይጠንቀቅ፤

ባልንጀራም በጓደኛው አይታመን።

5ባልንጀራ ባልንጀራውን ያታልላል፤

እውነትን የሚናገር የለም፤

ሐሰትን ይናገሩ ዘንድ ምላሳቸውን አሠልጥነዋል፤

ኀጢአትንም በማድረግ ራሳቸውን አድክመዋል።

6መኖሪያህ9፥6 ኤርምያስን ያመለክታል (በዕብራይስጡ በነጠላ ቍጥር ተጽፏል) በሽንገላ መካከል ነው፤

ከሽንገላቸውም የተነሣ ሊያውቁኝ አልፈቀዱም፤”

ይላል እግዚአብሔር

7ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“እነሆ፤ እንደ ብረት አነጥራቸዋለሁ፤ እፈትናቸዋለሁም፤

ስለ ሕዝቤ ኀጢአት፣

ከዚህ የተለየ ምን ማድረግ እችላለሁ?

8ምላሳቸው የሚገድል ቀስት ነው፤

በሽንገላ ይናገራል፤

ሁሉም ከባልንጀራው ጋር በፍቅር ይናገራል፤

በልቡ ግን ያደባበታል።

9ታዲያ ስለ እነዚህ ነገሮች ልቀጣቸው አይገባኝምን?”

ይላል እግዚአብሔር

“እንደዚህ ዐይነቱንስ ሕዝብ፣

አልበቀልምን?”

10ስለ ተራሮች አለቅሳለሁ፤ ዋይ ዋይ እላለሁ፤

በምድረ በዳ ስላሉትም መሰማሪያዎች ዐዝናለሁ።

ሰው የማያልፍባቸው ባድማ ሆነዋል፤

የከብቶች ጩኸት አይሰማም፤

የሰማይ ወፎች ሸሽተዋል፤

የዱር አራዊትም ጠፍተዋል።

11“ኢየሩሳሌምን የፍርስራሽ ክምር፣

የቀበሮም ጐሬ አደርጋታለሁ፤

የይሁዳንም ከተሞች፣

ሰው የማይኖርባቸው ባድማ አደርጋቸዋለሁ።”

12ይህን መረዳት የሚችል ጥበበኛ ሰው ማን ነው? እግዚአብሔር ገልጾለት ይህንስ ማስረዳት የሚችል ማን ነው? ምድሪቱስ ሰው እንደማያልፍበት በረሓ ለምን ጠፋች? ለምን ወና ሆነች?

13እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ይህ የሆነው የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተው ስላልታዘዙኝና ሥርዐቴን ስላልተከተሉ ነው። 14በዚህ ፈንታ፣ በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ አባቶቻቸው ያስተማሯቸውን በኣሊምን ተከተሉ።” 15ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ይህን ሕዝብ መራራ ምግብ አበላዋለሁ፤ የተመረዘንም ውሃ አጠጣዋለሁ። 16እነርሱንም ሆነ አባቶቻቸውን በማያውቋቸው ሕዝቦች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ እስካጠፋቸውም ድረስ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።”

17የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“እንግዲህ፤ አልቃሽ ሴቶች ጥሩ፤

ሥልጡን ሙሾ አውራጆች አስመጡ፤

18እነርሱ ፈጥነው ይምጡ፤

ዐይኖቻችን እንባ እስኪያጐርፉ፣

ሽፋሽፍቶቻችንም ውሃ እስኪያመነጩ፣

ስለ እኛ ሙሾ ያውርዱልን።

19እነሆ የዋይታ ድምፅ ከጽዮን ተሰምቷል፤ እንዲህም ይላል፤

‘ምንኛ ወደቅን!

ውርደታችንስ እንዴት ታላቅ ነው!

ቤቶቻችን ፈራርሰዋልና፤

አገራችንን ጥለን እንሂድ።’ ”

20እናንት ሴቶች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤

ጆሮቻችሁን ከአንደበቱ ለሚወጡት ቃላት ክፈቱ፤

ሴቶች ልጆቻችሁን ዋይታ፣

አንዳችሁም ሌላውን ሙሾ አስተምሩ።

21ሞት በመስኮቶቻችን ገብቷል፤

ወደ ምሽጎቻችንም ዘልቋል፤

ሕፃናትን ከየመንገዱ፣

ወጣቶችን ከየአደባባዩ ጠራርጎ ወስዷል።

22እንዲህ በሉ፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ ‘የሰዎች ሬሳ፣

በሜዳ እንደ ተጣለ ጕድፍ፣

ማንም እንደማይሰበስበው፣

ከዐጫጅ ኋላ እንደ ተተወ ቃርሚያ ይወድቃል።’ ”

23እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ጥበበኛ በጥበቡ አይታበይ፤

ኀያልም በኀይሉ አይመካ፤

ሀብታምም በሀብቱ አይኵራራ፤

24የሚመካ ግን፣

እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በማወቁና፣

በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣

በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣

እደሰታለሁና፤”

ይላል እግዚአብሔር

25እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሥጋቸውን ብቻ የተገረዙትን ሁሉ የምቀጣበት ጊዜ ይመጣል፤ 26እነርሱም ግብፅ፣ ይሁዳ፣ ኤዶም፣ አሞን፣ ሞዓብና ጠጕራቸው ዙሪያውን የሚከረከም የበረሓ9፥26 ወይም በበረሓ በተራራቁ ስፍራዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ሁሉ ናቸው፤ እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ በርግጥ የተገረዙ አይደሉምና፤ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው አልተገረዘም።”