ሰቈቃወ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሰቈቃወ 1:1-22

א አሌፍ

1 ይህ ምዕራፍ ጥቅሶቹ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምር፣ የመጀመሪያው ወይም የመጨረሻው መሥመር ትርጕም የሚሰጥ ቃል ወይም ዐረፍተ ነገር ያለው ግጥም ነው። 1በሕዝብ ተሞልታ የነበረችው ከተማ፣

እንዴት የተተወች ሆና ቀረች!

በሕዝቦች መካከል ታላቅ የነበረችው፣

እርሷ እንዴት እንደ መበለት ሆነች!

በአውራጃዎች መካከል ልዕልት የነበረችው፣

አሁን ባሪያ ሆናለች።

ב ቤት

2በሌሊት አምርራ ታለቅሳለች፤

እንባዋ በጕንጮቿ ላይ ይወርዳል፤

ከወዳጆቿ ሁሉ መካከል፣

የሚያጽናናት ማንም የለም፤

ባልንጀሮቿ ሁሉ ከድተዋታል፤

ጠላቶቿም ሆነዋል።

ג ጊሜል

3በመከራና በመረገጥ ብዛት

ይሁዳ ተማርካ ሄደች፤

በሕዝቦችም መካከል ተቀመጠች፤

የምታርፍበትንም ስፍራ ዐጣች፤

በጭንቀቷ መካከል ሳለች፣

አሳዳጆቿ ሁሉ አገኟት።

ד ዳሌት

4የጽዮን መንገዶች ያለቅሳሉ፤

በዓላቷን ለማክበር የሚመጣ የለምና፤

በበሮቿ ሁሉ የሚገባና የሚወጣ የለም፤

ካህናቷ ይቃትታሉ፤

ደናግሏ ክፉኛ ዐዝነዋል፤

እርሷም በምሬት ትሠቃያለች።

ה ሄ

5ባላጋሮቿ ገዦቿ ሆኑ፤

ጠላቶቿ ተመችቷቸዋል፤

ከኀጢአቷ ብዛት የተነሣ፣

እግዚአብሔር ከባድ ሐዘን አምጥቶባታል።

ልጆቿ በጠላት ፊት ተማርከው፣

ወደ ግዞት ሄደዋል።

ו ዋው

6የጽዮን ሴት ልጅ፣

ግርማ ሞገሷ ሁሉ ተለይቷታል፤

መሳፍንቷ፣

መሰማሪያ እንዳጣ ዋሊያ ናቸው፤

በአሳዳጆቻቸው ፊት፣

በድካም ሸሹ።

ז ዛይን

7በተጨነቀችባቸውና በተንከራተተችባቸው ቀናት፣

ኢየሩሳሌም በጥንት ዘመን የነበራትን፣

ሀብት ሁሉ ታስባለች፤

ሕዝቦቿ በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ፣

የረዳት ማንም አልነበረም፤

ጠላቶቿ ተመለከቷት፤

በመፈራረሷም ሣቁ።

ח ኼት

8ኢየሩሳሌም ከባድ ኀጢአት ሠርታለች፤

ስለዚህም የረከሰች ሆናለች፤

ያከበሯት ሁሉ ናቋት፤

ዕራቍቷን ሆና አይተዋታልና፤

እርሷ ራሷ ታጕረመርማለች፤

ወደ ኋላዋም ዘወር ብላለች።

ט ቴት

9ርኩሰቷ በቀሚሷ ላይ ታየ፤ ወደ ፊት የሚሆንባትን አላሰበችም፤

አወዳደቋ አስደንጋጭ ሆነ፤

የሚያጽናናትም አልነበረም፤

እግዚአብሔር ሆይ፤ መከራዬን

ተመልከት፤

ጠላት ድል አድርጓልና!”

י ዮድ

10ዮድ በሀብቷ ሁሉ ላይ፣

ጠላት እጁን ዘረጋ፤

ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ

የከለከልሃቸው፣

ጣዖት የሚያመልኩ አሕዛብ፣

ወደ መቅደሷ ሲገቡ አየች።

כ ካፍ

11እንጀራ በመፈለግ፣

ሕዝቧ ሁሉ በሥቃይ ይጮኻል፤

በሕይወት ለመኖር፣

የከበረ ሀብታቸውን በምግብ ይለውጣሉ፤

“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ አስበኝ፤ ተመልከተኝም፤

እኔ ተዋርጃለሁና።”

ל ላሜድ

12“እናንት መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ፤ ይህ ለእናንተ ምንም አይደለምን?

ተመልከቱ፤ እዩም፤

በጽኑ ቍጣው ቀን፣

እግዚአብሔር ያመጣብኝን፣

በእኔ ላይ የደረሰውን፣

የእኔን መከራ የመሰለ መከራ አለን?

מ ሜም

13“ከከፍታ ስፍራ እሳትን ላከ፤

ወደ ታች ወደ ዐጥንቶቼም ሰደደው፤

በእግሮቼ ላይ መረብ ዘረጋ፤

ወደ ኋላም ጣለኝ፤

ቀኑን ሙሉ በማድከም፣

ባዶ አድርጎ አስቀመጠኝ።

נ ኑን

14“ኀጢአቶቼ ቀንበር ሆኑ፤1፥14 አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ ቅጆች እንዲሁ ሲሆኑ ሰብዓ ሊቃናት ግን ኀጢአቶቼን ያለ ማቋረጥ ይከታተላል ይላል።

በእጆቹ አንድ ላይ ተገመዱ፤

በዐንገቴም ላይ ተጭነዋል፤

ኀይሌንም አዳከመ፤

ልቋቋማቸው ለማልችላቸው፣

እርሱ አሳልፎ ሰጠኝ።

ס ሳሜክ

15“በውስጤ ያሉትን ተዋጊዎች ሁሉ፣

እግዚአብሔር ተቃወመ፤

ጕልማሶቼን ለማድቀቅ፣

ሰራዊት በላዬ ላይ ጠራ1፥15 ወይም …በሚያደቅቅበት ጊዜ፣ ለእኔ ጊዜን ወሰነልኝ።

ድንግሊቱን የይሁዳ ሴት ልጅ፣

እግዚአብሔር በወይን መጭመቂያ ውስጥ ረገጣት።

ע ዐዪን

16“የማለቅሰው ስለ እነዚህ ነገሮች ነው፤

ዐይኖቼ በእንባ ተሞልተዋል፣

ሊያጽናናኝ የቀረበ፣

መንፈሴንም ሊያረጋጋ የሞከረ ማንም የለም፤

ጠላት በርትቷልና

ልጆቼ ተጨንቀዋል።”

פ ፌ

17ጽዮን እጆቿን ዘረጋች፤

የሚያጽናናትም የለም፤

ጎረቤቶቹ ጠላቶቹ እንዲሆኑ፣

እግዚአብሔር በያዕቆብ ላይ ትእዛዝ አውጥቷል፤

ኢየሩሳሌምም በመካከላቸው፣

እንደ ርኩስ ነገር ተቈጠረች።

צ ጻዲ

18እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤

እኔ ግን በትእዛዙ ላይ ዐመፅ አድርጌ ነበር፤

እናንተ ሕዝቦች ሁሉ ስሙ፤

መከራዬንም ተመልከቱ፤

ወይዛዝርቶቼና ጐበዛዝቶቼ፣

ተማርከው ሄደዋል።

ק ቆፍ

19“ወዳጆቼን ጠራኋቸው፤

እነርሱ ግን ከዱኝ፤

ካህናቶቼና ሽማግሌዎቼ፣

ሕይወታቸውን ለማትረፍ፣

ምግብ ሲፈልጉ፣

በከተማዪቱ ውስጥ ዐለቁ።

ר ሬሽ

20“አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ተጨንቄአለሁ!

በውስጤ ተሠቃይቼአለሁ፤

በልቤ ታውኬአለሁ፤

እጅግ ዐመፀኛ ሆኛለሁና፤

በውጭ ሰይፍ ይፈጃል፤

በቤትም ውስጥ ሞት አለ።

ש ሲን እና ሺን

21“ሰዎች የሥቃይ ልቅሶዬን ሰሙ፤

የሚያጽናናኝ ግን ማንም የለም፤

ጠላቶቼ ሁሉ ጭንቀቴን ሰሙ፤

አንተ ባደረግኸውም ደስ አላቸው፤

አቤቱ የተናገርሃት ቀን ትምጣ፤

እነርሱም እንደ እኔ ይሁኑ።

ת ታው

22“ክፋታቸው ሁሉ በፊትህ ይቅረብ፤

ከኀጢአቴ ሁሉ የተነሣ፣

በእኔ ላይ እንዳደረግህብኝ፣

በእነርሱም ላይ አድርግባቸው፤

የሥቃይ ልቅሶዬ በዝቷል፤

ልቤም ደክሟል።”