ማርቆስ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ማርቆስ 2:1-28

ኢየሱስ ሽባ ፈወሰ

2፥3-12 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥2-8ሉቃ 5፥18-26

1ኢየሱስ ከጥቂት ቀን በኋላ ወደ ቅፍርናሆም እንደ ተመለሰ፣ ወደ ቤት መግባቱን ሕዝቡ ሰማ። 2ስለዚህ ከበሩ ውጭ እንኳ ሳይቀር ስፍራ እስኪታጣ ድረስ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ሰበከላቸው። 3ጥቂት ሰዎችም አንድ ሽባ በአራት ሰዎች አሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። 4ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ኢየሱስ ወዳለበት መቅረብ ስላልቻሉ፣ የቤቱን ጣራ እርሱ ባለበት በኩል ነድለው ቀዳዳ በማበጀት ሽባው የተኛበትን ዐልጋ በዚያ አወረዱ። 5ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አንተ ልጅ፣ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል!” አለው።

6በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ ጸሐፍት ስለዚህ ነገር በልባቸው እያሰላሰሉ፣ 7“ይህ ሰው እንዴት እንዲህ ይላል? በአምላክ ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ እኮ ነው! ከአንዱ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማን ኀጢአትን ሊያሰተሰርይ ይችላል?” ብለው አሰቡ።

8ኢየሱስም ወዲያው በልባቸው የሚያስቡትን በመንፈሱ ተረድቶ፣ “እንዴት እንዲህ ታስባላችሁ? 9ሽባውን፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና፣ ‘ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል? 10ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ” በማለት ሽባውን፣ 11“ተነሥተህ ዐልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። 12እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ዐልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ በስፍራው የነበሩትም ሁሉ በሁኔታው በመደነቅ፣ “የዚህ ዐይነት ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም!” በማለት ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀረቡ።

የሌዊ መጠራት

2፥14-17 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥9-13ሉቃ 5፥27-32

13ኢየሱስም ዳግም ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወጣ፤ ሕዝቡም በብዛት ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም አስተማራቸው። 14በዚያም ሲያልፍ የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን በቀረጥ መቀበያው ስፍራ ተቀምጦ አየውና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።

15በማቴዎስ ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች ተከትለውት ስለ ነበር፣ ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይመገቡ ነበር። 16ከፈሪሳውያን ወገን የነበሩ ጸሐፍት ከኀጢአተኞችና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሲበላ ባዩት ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋር ለምን ይበላል?” ሲሉ ጠየቋቸው።

17ኢየሱስም የሚናገሩትን ሰምቶ፣ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም፤ እኔ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ወደ ንስሓ ልጠራ አልመጣሁም” አላቸው።

ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ

2፥18-22 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥14-17ሉቃ 5፥33-38

18የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር፤ አንዳንድ ሰዎችም መጥተው ኢየሱስን፣ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት።

19ኢየሱስም፣ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎቹ ሊጾሙ ይችላሉን? ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሊጾሙ አይችሉም፤ 20ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወቅት ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ግን ይጾማሉ።

21“በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ጨርቅ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፣ አዲሱ ጨርቅ አሮጌውን ይቦጭቀዋል፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሰፋል። 22እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ የሚያስቀምጥ የለም፤ ይህ ከተደረገማ የወይን ጠጁ አቍማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም አቍማዳውም ይበላሻሉ። ስለዚህ አዲስ የወይን ጠጅ መቀመጥ ያለበት በአዲስ አቍማዳ ነው።”

ኢየሱስ የሰንበት ጌታ ነው

2፥23-28 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥1-8ሉቃ 6፥1-5

3፥1-6 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥9-14ሉቃ 6፥6-11

23በሰንበት ቀን ኢየሱስ በዕርሻ መካከል ሲያልፍ፣ አብረውት በመጓዝ ላይ የነበሩት ደቀ መዛሙርቱ እሸት ይቀጥፉ ጀመር። 24ፈሪሳውያንም፣ “እነሆ፤ በሰንበት ቀን ለምን የተከለከለ ነገር ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት።

25እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት በተራበና የምግብ ፍላጎት በጸናበት ጊዜ አብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋር ያደረገውን አላነበባችሁምን? 26በሊቀ ካህናቱ በአብያታር ዘመን ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፣ ካህናት ብቻ እንዲበሉት የተፈቀደውን የተቀደሰ ኅብስት ራሱ በልቶ አብረውት ለነበሩትም ሰዎች ሰጣቸው።”

27ደግሞም እንዲህ አላቸው፤ “ሰንበት ለሰው ተፈጠረ እንጂ፣ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም፤ 28ስለዚህ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታዋ ነው።”