መዝሙር 18 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

መዝሙር 18:1-50

መዝሙር 18

የድል መዝሙር

18 ርእስ-50 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 22፥1-51

ለመዘምራን አለቃ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር፤ ይህም እግዚአብሔር ከሳዖልና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ በታደገው ጊዜ፣ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል የዘመረው ነው፤

1ጕልበቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ እወድድሃለሁ።

2እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤

አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፤

እርሱ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና18፥2 ቀንድ በዚህ ቦታ ብርታትን ያመለክታል። ዐምባዬ ነው።

3ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤

ከጠላቶቼም እድናለሁ።

4የሞት ገመድ ዐነቀኝ፤

የጥፋት ጐርፍም አጥለቀለቀኝ።

5የሲኦል18፥5 ወይም የመቃብር ገመድ ተጠመጠመብኝ፤

የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ።

6በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤

እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤

እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤

ጩኸቴም ከፊቱ ደረሰ፤ ወደ ጆሮውም ገባ።

7ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤

የተራሮችም መሠረት ተናጋ፤

ጌታ ተቈጥቷልና ተንቀጠቀጡ።

8ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤

የሚባላ እሳት ከአፉ፤

የፍም ነበልባል ከእርሱ ፈለቀ።

9ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤

ከእግሩም በታች ጥቍር ደመና ነበረ።

10በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤

በነፋስም ክንፍ መጠቀ።

11ጨለማን መሰወሪያው፣ በዙሪያውም አጐበሩ አደረገው፤

በዝናብ ዐዘል ጥቍር ደመናም ተሸፈነ።

12በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ፣

ደመናት፣ የበረዶ ድንጋይና መብረቅ ወጡ።

13እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤

ልዑልም ድምፁን አስተጋባ።18፥13 አንዳንድ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆችና ሰብዓ ሊቃናት (በተጨማሪ 2ሳሙ 22፥14 ይመ) እንዲሁ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ግን …አስተጋባ፤ በድንጋይ ዝናብ በድንገተኛ መብረቅ መካከል የሚለውን ይጨምራሉ።

14ፍላጻውን አስፈንጥሮ በተናቸው፤

መብረቅ አዥጐድጕዶ አሳደዳቸው።

15እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተግሣጽህ የተነሣ፣

ከአፍንጫህም እስትንፋስ የተነሣ፣

የባሕር ወለል ተገለጠ፤

የዓለምም መሠረት ዕራቍቱን ቀረ።

16ከላይ እጁን ወደ ታች ዘርግቶ ያዘኝ፤

ከብዙ ጥልቅ ውሃም አወጣኝ፤

17ከኀያላን ጠላቶቼ አዳነኝ፤

ከእኔ ከሚበረቱ ባላንጣዎቼም ታደገኝ።

18እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤

እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ።

19ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤

ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ።

20እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መልሶልኛል፤

እንደ እጄ ንጽሕናም ከፍሎኛል፤

21የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤

አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም።

22ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤

ሥርዐቱን ከፊቴ አላራቅሁም።

23በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤

ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።

24እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን፣

በፊቱ እንደ እጄም ንጽሕና ከፍሎኛል።

25ከታማኙ ጋር ታማኝ ትሆናለህ፤

እንከን ከሌለበት ጋር ያለ እንከን ትሆናለህ፤

26ከንጹሑ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤

ለጠማማው አንተ ትጠምበታለህ።

27አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤

ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ።

28እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴን ታበራለህ፤

አምላኬ ሆይ፤ ጨለማዬን ብርሃን ታደርገዋለህ።

29በአንተ ጕልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤18፥29 ወይም …በመሰናክል ውስጥ መሮጥ እችላለሁ

በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ።

30የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤

የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው።

መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ፣

እርሱ ጋሻ ነው።

31ከእግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ?

ከአምላካችንስ በቀር ዐምባ ማን ነው?

32ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣

መንገዴንም የሚያቃና እግዚአብሔር ነው።

33እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያደርጋል፤

በከፍታዎችም ላይ ያቆመኛል።

34እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል፤

ክንዴም የናስ ቀስት መገተር ይችላል።

35የድል ጋሻ ሰጥተኸኛል፤

ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች፤

ዝቅ ብለህም ከፍ አደረግኸኝ።

36ከሥሬ ያለውን ስፍራ ለአረማመዴ አሰፋህልኝ፤

እግሬም አልተንሸራተተም።

37ጠላቶቼን አሳድጄ ያዝኋቸው፤

እስኪጠፉም ወደ ኋላዬ አልተመለስሁም።

38እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቀቅኋቸው፤

ከእግሬም ሥር ወደቁ።

39አንተ ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፤

ባላንጦቼ እግሬ ላይ እንዲደፉ አደረግህ።

40ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው እንዲሸሹ አደረግህ፤

እኔም የሚጠሉኝን አጠፋኋቸው።

41ለርዳታ ጮኹ፤ የሚያስጥላቸው ግን አላገኙም፤

ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱም አልመለሰላቸውም።

42ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ አደቀቅኋቸው፤

እንደ መንገድ ላይ ጭቃም አውጥቼ ጣልኋቸው።

43ከሕዝብ ግርግር አወጣኸኝ፤

የሕዝቦች መሪ አድርገህ አስቀመጥኸኝ፤

የማላውቀውም ሕዝብ ተገዛልኝ።

44ትእዛዜን እንደ ሰሙ ይታዘዙልኛል፤

ባዕዳንም በፊቴ ዐንገት ደፉ።

45ባዕዳን በፍርሀት ተዋጡ፤

ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ።

46እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐምባዬ ይባረክ፤

ያዳነኝ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።

47እርሱ በቀሌን የሚመልስልኝ፣

ሕዝቦችንም የሚያስገዛልኝ አምላክ ነው፤

48ከጠላቶቼም የሚታደገኝ እርሱ ነው።

አንተ ከባላንጦቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤

ከጨካኞች አዳንኸኝ።

49እግዚአብሔር ሆይ፤ ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤

ስምህንም በመዝሙር እወድሳለሁ።

50እርሱ ላነገሠው ታላላቅ ድሎችን ይሰጣል፤

ጽኑ ፍቅሩንም ለቀባው፣

ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይገልጣል።