ሕዝቅኤል 20 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ሕዝቅኤል 20:1-49

ዐመፀኛዪቱ እስራኤል

1በሰባተኛው ዓመት፣ በአምስተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን ከእስራኤል ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፤ በፊቴም ተቀመጡ።

2የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 3“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሐሳቤን ልትጠይቁ መጣችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ ከእኔ ጠይቃችሁ እንድትረዱ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

4“የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህን ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? በውኑ ለፍርድ ታቀርባቸዋለህን? የቀድሞ አባቶቻቸውን አስጸያፊ ተግባር ግለጥላቸው፤ 5እንዲህም በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፣ ለያዕቆብ ቤት ዘር እጄን አንሥቼ ማልሁላቸው፤ በግብፅም ራሴን ገለጥሁላቸው። እጄንም አንሥቼ፣ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው።” 6በዚያን ቀን፣ ከግብፅ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው። 7እኔም፣ “እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብፅ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” አልኋቸው።

8“ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብፅንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብፅ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር። 9ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብፅ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ። 10ስለዚህ ከግብፅ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው። 11ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው። 12ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።

13“ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር። 14ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ። 15ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤ 16ምክንያቱም ሕጎቼን ተላልፈዋል፤ ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሰንበቴንም አርክሰዋል፤ ልባቸው ከጣዖቶቻቸው ጋር ተጣብቋልና። 17እኔ ግን በርኅራኄ ተመለከትኋቸው እንጂ አላጠፋኋቸውም፤ በምድረ በዳም አልፈጀኋቸውም። 18ለልጆቻቸው በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፤ “የአባቶቻችሁን ሥርዐት አትከተሉ፤ ወጋቸውን አትጠብቁ፤ ራሳችሁንም በጣዖቶቻቸው አታርክሱ። 19እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ ሥርዐቴን ተከተሉ፤ ሕጌንም ለመጠበቅ ትጉ። 20በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆን ዘንድ ሰንበቴን የተቀደሰ ቀን አድርጉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁም ታውቃላችሁ።”

21“ ‘ልጆቻቸው ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልተከተሉም፤ ሕጌን ለመጠበቅ አልተጉም፤ ሰንበቴንም አረከሱ። እኔም በምድረ በዳ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ፤ ቍጣዬንም አወርድባቸዋለሁ ብዬ ነበር። 22ነገር ግን ከግብፅ ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ እጄን ሰበሰብሁ። 23ደግሞም በአሕዛብ መካከል እንደምበትናቸውና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደማፈልሳቸው በምድረ በዳ እጄን አንሥቼ በፊታቸው ማልሁ፤ 24ምክንያቱም ሥርዐቴን አቃለሉ፤ ሰንበቴን አረከሱ እንጂ ሕጌን አልጠበቁም፤ ዐይናቸውም ከአባቶቻቸው ጣዖታት ጋር ተጣብቋል። 25እኔም መልካም ላልሆነ ሥርዐትና በሕይወት ለማይኖሩበት ሕግ አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ 26እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንዲያውቁ፣ አስደነግጣቸውም ዘንድ በእሳት በሚያቀርቡት የበኵር ልጅ መሥዋዕት እንዲረክሱ አደረግኋቸው።’20፥26 ወይም የበኵር ልጅን ሁሉ በእሳት ውስጥ በማሳለፍ

27“ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አባቶቻችሁ እኔን በመተው በዚህ ደግሞ አቃለሉኝ፤ 28ልሰጣቸው ወደማልሁላቸው ምድር ባስገባኋቸው ጊዜ፣ ከፍ ያለውን ኰረብታ ሁሉና የለመለመውን ዛፍ ሁሉ ተመለከቱ፤ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ፤ ቍርባናቸውን በማቅረብ ቍጣዬን አነሣሡ፤ መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣናቸውን ዐጠኑ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውንም አፈሰሱ። 29እኔም፣ የምትሄዱበት ይህ ከፍታ ቦታ ምንድን ነው?’ ” አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ20፥29 ባማ ማለት ከፍታ ቦታ ማለት ነው ተብሎ ይጠራል።

ቅጣትና ምሕረት

30“ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አባቶቻችሁ እንዳደረጉት ራሳችሁን ታረክሳላችሁን? በረከሱ ምስሎቻቸው ምኞት ትቃጠላላችሁን? 31ቍርባናችሁን በምታቀርቡበት ጊዜ ልጆቻችሁን ለእሳት በመዳረግ20፥31 ወይም ልጆቻችሁን በእሳት ውስጥ በማሳለፍ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ሁሉ እየረከሳችሁ ናችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ታዲያ የእኔን ሐሳብ እንድትጠይቁ ልፍቀድላችሁን? በሕያውነቴ እምላለሁ እንድትጠይቁኝ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

32“ ‘እናንተም፣ “ለዕንጨትና ለድንጋይ እንደሚሰግዱ እንደ አሕዛብ፣ በዓለምም እንደሚኖረው ሕዝብ ሁሉ እንሁን” አላችሁ፤ ነገር ግን በልባችሁ ያሰባችሁት ከቶ አይሆንላችሁም። 33በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ መዓትንም በማፍሰስ በላያችሁ እነግሣለሁ። 34ከአሕዛብ መካከል አወጣችኋለሁ፤ በብርቱ ክንድና በተዘረጋች እጅ፣ መዓትንም በማፍሰስ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች ሁሉ እሰበስባችኋለሁ። 35ወደ አሕዛብ ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ፤ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። 36በግብፅ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ፣ ከእናንተም ጋር እፋረዳለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር37ከበትሬ በታች አሳልፋችኋለሁ፤ ከቃል ኪዳኔም ጋር አጣብቃችኋለሁ። 38በእኔ ላይ ያመፁትንና የበደሉኝን ከመካከላችሁ አስወግዳለሁ፤ ከሚኖሩበት አገር አወጣቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

39“ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለ እናንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የማትሰሙኝ ከሆነ፣ እያንዳንዳችሁ ሂዱና ለጣዖቶቻችሁ ስገዱ! ነገር ግን በቍርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን ከእንግዲህ አታረክሱም። 40በቅዱሱ ተራራዬ፣ ከፍ ባለው የእስራኤል ተራራ ላይ በዚያ ምድር የእስራኤል ቤት ሁሉ ያመልከኛልና፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እኔም በዚያ እቀበላቸዋለሁ። ቍርባናችሁንና በኵራታችሁን ከተቀደሱ መሥዋዕቶቻችሁ ሁሉ ጋር በዚያ እሻለሁ። 41ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ። 42ለአባቶቻችሁ ልሰጥ እጄን አንሥቼ ወደማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር በማስገባችሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 43በዚያም መንገዳችሁንና ራሳችሁን ያረከሳችሁበትን ተግባር ሁሉ ታስታውሳላችሁ፤ በፈጸማችሁትም ክፋት ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 44የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ብልሹ ተግባራችሁ ሳይሆን፣ ስለ ስሜ ስል በምጐበኛችሁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

በደቡቡ አገር ላይ የተነገረ ትንቢት

45የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 46“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ደቡብ አዙር፤ በደቡብ ላይ ቃል ተናገር፤ በደቡብ አገር ደን ላይም ትንቢት ተንብይ። 47ለደቡቡ ደን እንዲህ በል፤ ‘የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በአንተ ላይ እሳት ልለኵስ ነው፤ እሳቱ የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍህን ሁሉ ይበላል፤ የሚንቦገቦገው ነበልባሉም አይጠፋም፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ያለውን ፊት ሁሉ ይለበልባል። 48ሰው ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንዳነደድሁት ያያል፤ የሚያጠፋውም የለም።’ ”

49እኔም፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፣ ‘ተምሳሌት ብቻ ይመስላል’ ይሉኛል” አልሁ።