2 ጢሞቴዎስ 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ጢሞቴዎስ 3:1-17

ክሕደት በመጨረሻዎቹ ቀናት

1ነገር ግን በመጨረሻው ዘመን የሚያስጨንቅ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ። 2ሰዎች ራሳቸውን የሚወድዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወድዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ 3ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወድዱ፣ 4ከዳተኞች፣ ችኵሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወድዱ ይሆናሉና። 5ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል። ከእነዚህ ራቅ።

6እነርሱም በየቤቱ ሾልከው እየገቡ የኀጢአት ብዛት የተጫናቸውን፣ በተለያየ ክፉ ምኞት ውስጥ ገብተው የሚዋልሉ መንፈሰ ደካማ ሴቶችን የሚያጠምዱ ናቸው፤ 7እንደነዚህ ያሉ ሴቶች ሁልጊዜ ይማራሉ፤ ነገር ግን እውነትን ወደ ማወቅ ፈጽሞ ሊደርሱ አይችሉም። 8ኢያኔስና ኢያንበሬስ ሙሴን እንደ ተቃወሙት፣ እነዚህ አእምሯቸው የጠፋባቸውና ከእምነት የተጣሉ ሰዎች ደግሞ እውነትን ይቃወማሉ። 9ይሁን እንጂ አይሳካላቸውም፤ ምክንያቱም የእነዚያ ሰዎች ሞኝነት እንደ ተገለጠ ሁሉ፣ የእነዚህም ለሁሉ ግልጽ ይሆናል።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ዐደራ

10አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ ዐላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና ጽናቴን ሁሉ ታውቃለህ፤ 11ስደቴንና መከራዬን፣ በአንጾኪያና በኢቆንዮን፣ በልስጥራንም የደረሰብኝን ሁሉ፣ የታገሥሁትንም ስደት ታውቃለህ፤ ጌታ ግን ከእነዚህ ሁሉ አዳነኝ። 12በርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወድዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። 13ክፉዎችና አታላዮች ግን እየሳቱና እያሳቱ፣ በክፋትም ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ። 14አንተ ግን በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና፤ ይህን ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ 15ከሕፃንነትህም ጀምረህ በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል። 16ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ 17ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።