2 ሳሙኤል 19 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

2 ሳሙኤል 19:1-43

1ለኢዮአብ፣ “ንጉሡ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም እያለቀሰ እያዘነ ነው” ተብሎ ተነገረው። 2ንጉሡ፣ “ስለ ልጁ ዐዝኗል” መባሉን በዚያ ቀን ሰራዊቱ ሰምቶ ስለ ነበር፣ የዚያ ዕለት ድል በመላው ሰራዊት ዘንድ ወደ ሐዘን ተለውጦ ዋለ። 3በዚያችም ዕለት ከጦርነት ሸሽቶ በኀፍረት እየተሸማቀቀ ወደ ከተማ እንደሚገባ ሰው ሕዝቡም ተሸማቆ ወደ ከተማ ገባ። 4ንጉሡ ፊቱን ሸፍኖ፣ “ልጄ አቤሴሎም ሆይ፤ ልጄን! ወየው ልጄን!” እያለ ጮኸ።

5ከዚያም ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ገብቶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን፣ የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን፣ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ሕይወት ያተረፉትን ሰዎች ሁሉ ዛሬ አሳፍረሃቸዋል። 6የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህን ትጠላለህ፤ የጦር አዛዦችህና ወታደሮቻቸው ለአንተ ምንህም እንዳይደሉ ይኸው ዛሬ ግልጽ አድርገሃል፤ ዛሬ አቤሴሎም በሕይወት ኖሮ እኛ ሁላችን ዐልቀን ቢሆን ደስ እንደሚልህ በዛሬው ዕለት ለማየት በቅቻለሁ። 7በል አሁን ተነሥተህ ውጣና ሰዎችህን አበረታታ፤ ባትወጣ ግን በዚች ሌሊት አንድም ሰው አብሮህ እንደማይሆን በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ይህ ደግሞ ከልጅነትህ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከደረሰብህ ክፉ ነገር ሁሉ የባሰ መከራ ያስከትልብሃል።” 8ስለዚህ ንጉሡ ተነሥቶ በበሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ለሕዝቡም፣ “እነሆ ንጉሡ በበሩ አጠገብ ተቀምጧል” ተብሎ በተነገረ ጊዜ ሕዝቡ በሙሉ ወደ ንጉሡ መጣ።

ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ

በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ወደየቤታቸው ሸሽተው ነበር።

9በመላው የእስራኤል ነገዶችም፣ ሕዝቡ እንዲህ እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር፤ “ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ አውጥቶናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ የታደገን እርሱ ነው፤ አሁን ግን በአቤሴሎም ምክንያት ከአገር ሸሽቶ ሄዷል፤ 10በላያችን ሆኖ እንዲገዛን የቀባነው አቤሴሎም ደግሞ በጦርነት ሞቷል፤ ታዲያ ንጉሡን የመመለሱን ጕዳይ ለምንድን ነው ዝም የምትሉት?”

11ንጉሥ ዳዊት ወደ ካህናቱ ወደ ሳዶቅና ወደ አብያታር እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፤ “የእስራኤል ሽማግሌዎችን እንዲህ በሏቸው አለ፤ ‘በመላው እስራኤል የሚባለው ሁሉ ለንጉሡ ባለበት የደረሰው ስለሆነ፣ ንጉሡን ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ? 12እናንተ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ወንድሞቼ ናችሁ፤ ታዲያ ንጉሡን ለመመለስ እንዴት የመጨረሻ ሰዎች ትሆናላችሁ?’ 13አሜሳይንም፣ ‘አንተስ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? ከአሁን ጀምሮ እስከ ሕይወትህ ፍጻሜ በኢዮአብ ምትክ የሰራዊቴ አዛዥ ባላደርግህ፣ እግዚአብሔር ክፉ ያድርግብኝ፣ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ’ ብላችሁ ንገሩት።”

14እርሱም የይሁዳን ሰዎች ልብ ሁሉ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ ማረከው፤ እነርሱም “አንተም ሰዎችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት። 15ከዚያም ንጉሡ ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ።

በዚህ ጊዜ የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ተቀብለው ዮርዳኖስን ለማሻገር እስከ ጌልገላ ድረስ መጥተው ነበር። 16የብራቂም ሰው የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ሆኖ ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ፈጥኖ ወረደ። 17ከእርሱም ጋር አንድ ሺሕ ብንያማውያን፣ እንዲሁም የሳኦል ቤተ ሰብ አገልጋይ ሲባ ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከሃያ አሽከሮቹ ጋር ሆኖ አብረውት ነበሩ። ከዚያም ንጉሡ ወዳለበት ወደ ዮርዳኖስ በጥድፊያ ወረዱ። 18የንጉሡን ቤተ ሰው ለማምጣትና እርሱ የሚፈልገውንም ሁሉ ለማድረግ በመልካው ተሻገሩ።

የጌራ ልጅ ሳሚ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ በንጉሡም ፊት ተደፍቶ፣ 19እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ በደሌን አይቍጠርብኝ፤ ንጉሥ ጌታዬ ከኢየሩሳሌም በወጣህባት ዕለት የፈጸምሁትን ስሕተት እርሳው፤ ከአእምሮህም አውጣው። 20እኔ አገልጋይህ ኀጢአት መሥራቴን ዐውቃለሁና፤ ዛሬ ግን ጌታዬን ንጉሡን ለመቀበል ከዮሴፍ ቤት ሁሉ የመጀመሪያ ሆኜ እነሆ መጥቻለሁ።”

21ከዚያም የጽሩያ ልጅ አቢሳ፣ “ሳሚ በእግዚአብሔር የተቀባውን የረገመ ስለሆነ፣ መሞት አይገባውምን?” አለ።

22ዳዊትም፣ “እናንት የጽሩያ ልጆች፣ እናንተንና እኔን ምን የሚያገናኘን ነገር አለ? ዛሬ ጠላት ሆናችሁኛል! ማንስ ቢሆን ዛሬ በእስራኤል ዘንድ ሰው መሞት አለበት? እኔ በእስራኤል ላይ ንጉሥ መሆኔን ያወቅሁበት ቀን አይደለምን?” ብሎ መለሰ። 23ስለዚህ ንጉሡ ሳሚን፣ “አትሞትም” አለው፤ ይህንም ንጉሡ በመሐላ አጸናለት።

24የሳኦል ልጅ ሜምፊቦስቴም ንጉሡን ለመቀበል ወረደ። ንጉሡ ከተሰደደበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ተመለሰበት ዕለት ድረስ ለእግሩ ተገቢውን ጥንቃቄ አላደረገም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም ነበር። 25እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

26እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፣ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ ሲባ አታለለኝ። 27በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የባሪያህን ስም አጥፍቷል፤ መቼም ንጉሥ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንህ ደስ ያለህን ሁሉ አድርግ። 28የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን ባሪያህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”

29ንጉሡም፣ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ ዕርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው።

30ሜምፊቦስቴም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።

31እንዲሁም ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ዮርዳኖስን ተሻገረ። 32በዚያን ጊዜ ቤርዜሊ በዕድሜ የገፋ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ እጅግ ባለጠጋ ስለ ነበረም ንጉሡ በመሃናይም ሳለ የሚመገበውን አምጥቶለት ነበር። 33ንጉሡም ቤርዜሊን፣ “ከእኔ ጋር ተሻገርና በኢየሩሳሌም አብረኸኝ ኑር፤ እኔ እመግብሃለሁ” አለው።

34ቤርዜሊ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምሄደው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው? 35እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ ደግና ክፉውን መለየት እችላለሁ? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንም መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል? 36አገልጋይህ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከንጉሡ ጋር ጥቂት መንገድ ይሄዳል፤ ነገር ግን ንጉሡ በዚህ ሁኔታ ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው? 37በገዛ ከተማዬ ሞቼ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እቀበር ዘንድ፣ አገልጋይህን አሰናብተውና ይመለስ፤ ነገር ግን አገልጋይህ ከመዓም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት።” 38ንጉሡም፣ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገራል፤ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ከእኔ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለአንተም አደርግልሃለሁ” አለው።

39ስለዚህም ሕዝቡ በሙሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ከዚያ በኋላም ንጉሡ ተሻገረ። ንጉሡ ቤርዜሊን ስሞ መረቀው፤ ቤርዜሊም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

40ንጉሡ ወደ ጌልጌላ ሲሄድ፣ ከመዓም አብሮት ሄደ። የይሁዳ ሰራዊት በሙሉ እንዲሁም ግማሹ የእስራኤል ሰራዊት ንጉሡን አጅበው አሻገሩት።

41ወዲያውም የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ መጥተው፣ “ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን በሹልክታ ለብቻቸው ይዘው እርሱንና ቤተ ሰውን ከተከታዮቹ ጋር ዮርዳኖስን ለምን አሻገሩ?” አሉት።

42የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፣ ለእስራኤል ሰዎች፣ “ይህን ያደረግነው ንጉሡ የቅርብ ዘመዳችን ስለሆነ ነው፤ ታዲያ ይህ እናንተን የሚያስቈጣ ነው? እኛ ከንጉሡ ተቀብለን አንዳች በልተናልን? ለራሳችንስ ምን የወሰድነው ነገር አለ?” አሏቸው።

43ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች፣ “እኛ እኮ ከንጉሡ ዐሥር እጅ ድርሻ አለን፤ ከዚህም በተጨማሪ በዳዊት ላይ ከእናንተ ይልቅ እኛ የበለጠ መብት አለን፤ ታዲያ እኛን የናቃችሁን ስለ ምንድን ነው? ንጉሣችን እንዲመለስ በመጀመሪያ የጠየቅነው እኛ አይደለንምን?” አሉ።

ነገር ግን የይሁዳ ሰዎች የሰጡት መልስ የእስራኤል ሰዎች ከሰጡት መልስ ይልቅ እጅግ የከረረ ነበር።