1 ተሰሎንቄ 2 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

1 ተሰሎንቄ 2:1-20

የጳውሎስ አገልግሎት በተሰሎንቄ

1ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ የመጣነው ለከንቱ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 2እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ፣ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን። 3የምናቀርበው ልመና ከስሕተት ወይም ከክፉ ዐላማ ወይም እናንተን ለማታለል ከመፈለግ የመነጨ አይደለም። 4ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ብለን አይደለም። 5የሽንገላ ቃል ከቶ እንዳልተናገርን ወይም ሥሥትን ለመሸፈን ብለን አስመሳዮች እንዳልሆንን ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው። 6ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንባችሁ ነበር፤ 7ነገር ግን እናት ልጇን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን።

8የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ። 9ወንድሞች ሆይ፤ ጥረታችንንና ድካማችንን ታስታውሳላችሁ፤ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እየሠራን ወንጌል ሰበክንላችሁ።

10በእናንተ በምታምኑት መካከል ሳለን እንዴት በቅድስና፣ በጽድቅ እንዲሁም ያለ ነቀፋ ሆነን እንደ ኖርን እናንተም እግዚአብሔርም ምስክሮች ናችሁ። 11አባት ለገዛ ልጆቹ እንደሚሆን እኛም ለእያንዳንዳችሁ የቱን ያህል እንደ ሆንን ታውቃላችሁና፤ 12ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትኖሩ ዘንድ አበረታታናችሁ፤ አጽናናናችሁ፤ አጥብቀንም ለመንናችሁ።

13ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእናንተ በምታምኑት ዘንድ በርግጥ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ እናመሰግናለን። 14ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን በይሁዳ የሚገኙትን የእግዚአብሔርን አብያተ ክርስቲያናት መስላችኋል፤ እነዚያ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፣ እናንተም ከገዛ ወገኖቻችሁ መከራን ተቀብላችኋል። 15እነርሱ ጌታ ኢየሱስንና ነቢያትን ገደሉ፤ እኛንም አሳደዱን፤ እግዚአብሔርንም ደስ አላሰኙትም፤ የሰውም ሁሉ ፀር ሆኑ፤ 16ይኸውም ይድኑ ዘንድ ለአሕዛብ እንዳንናገር ለመከልከል ነው፤ በዚህ ሁኔታ ኀጢአታቸውን ሁልጊዜ በራሳቸው ላይ እስከ መጨረሻው እያከማቹ ይሄዳሉ። ቍጣውም በእነርሱ ላይ ያለ ልክ መጥቷል2፥16 ወይም በሙላት መጥቷል

ጳውሎስ የተሰሎንቄን ሰዎች ለማየት የነበረው ናፍቆት

17ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፤ እኛ በልባችን ሳይሆን በአካል ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ብንለይም፣ ለእናንተ ካለን ታላቅ ናፍቆት የተነሣ ፊታችሁን ለማየት ብርቱ ጥረት አደረግን። 18ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን አዘገየኝ። 19ጌታችን ኢየሱስ ሲመጣ በእርሱ ፊት ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም አክሊላችን ማን ነው? እናንተ አይደላችሁምን? 20በርግጥ እናንተ ክብራችንም ደስታችንም ናችሁ።