ዮናስ 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዮናስ 1:1-17

ዮናስ ከእግዚአብሔር ኰበለለ

1የእግዚአብሔር ቃል ወደ አማቴ ልጅ ወደ ዮናስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 2“ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ፣ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋቷ በእኔ ፊት ወጥቷልና።”

3ዮናስ ግን ከእግዚአብሔር ፊት ኰበለለ፤ ወደ ተርሴስም ለመሄድ ተነሣ። ወደ ኢዮጴ ወረደ፤ ወደዚያው ወደ ተርሴስ የምትሄድ መርከብም አገኘ። የጕዞውንም ዋጋ ከከፈለ በኋላ፣ ከእግዚአብሔር ፊት ወደ ተርሴስ ለመኰብለል በመርከቢቱ ተሳፈረ። 4እግዚአብሔርም በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን ላከ፤ ከባድ ማዕበልም ተነሥቶ መርከቢቱን አንገላታት፤ ልትሰበርም ተቃረበች። 5መርከበኞቹ ሁሉ ፈሩ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደ አምላኩ ጮኸ፤ የመርከቢቱም ክብደት እንዲቀልል፣ በውስጧ የነበረውን ዕቃ ወደ ባሕሩ ጣሉት።

ዮናስ ግን ወደ መርከቢቱ ታችኛ ክፍል ወርዶ ተኛ፤ በከባድም እንቅልፍ ላይ ነበር። 6የመርከቢቱም አዛዥ ወደ እርሱ ሄዶ፣ “እንዴት ትተኛለህ? ተነሥና አምላክህን ጥራ እንጂ፤ ምናልባትም ያስበንና ከጥፋት ያድነን ይሆናል” አለው።

7ከዚያም መርከበኞቹ እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንደ መጣብን ለማወቅ፣ ኑ ዕጣ እንጣጣል” ተባባሉ። ዕጣም ተጣጣሉ፤ ዕጣውም በዮናስ ላይ ወደቀ።

8ከዚያም፣ “ይህ ሁሉ አስጨናቂ ነገር በማን ምክንያት እንደ መጣብን ንገረን፤ ሥራህ ምንድን ነው? ከወዴትስ መጣህ? አገርህስ የት ነው? ከየትኛውስ ሕዝብ ነህ?” አሉት።

9እርሱም፣ “እኔ ዕብራዊ ነኝ፤ የብስንና ባሕርን የፈጠረውን የሰማይን አምላክ እግዚአብሔርን አመልካለሁ” አለ።

10እርሱ አስቀድሞ ነግሯቸው ስለ ነበር፣ ከእግዚአብሔር እንደ ኰበለለ ዐወቁ፣ ስለዚህም በሁኔታው በመደንገጥ፣ “ይህ ያደረግኸው ምንድን ነው?” አሉት።

11የባሕሩም ማዕበል እጅግ እየበረታ ስለ ሄደ፣ “ባሕሩ ጸጥ እንዲልልን በአንተ ላይ ምን ብናደርግ ይሻላል?” አሉት።

12እርሱም፣ “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደ መጣባችሁ ዐውቃለሁ፤ አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይላል” አላቸው።

13ሰዎቹ ግን ባላቸው ኀይል እየቀዘፉ ወደ የብስ ለመጠጋት ሞከሩ፤ ይሁን እንጂ አልቻሉም፤ ባሕሩ የባሰ ይናወጥ ነበርና። 14እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ በዚህ ሰው ነፍስ ምክንያት አታጥፋን፤ የዚህ ንጹሕ ሰው ደምም በእኛ ላይ አይሁን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የወደድኸውን አድርገሃልና” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 15ከዚያም ዮናስን ይዘው ወደ ባሕሩ ጣሉት፤ ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ። 16ሰዎቹም እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትም አቀረቡ፤ ለእርሱም ስእለትን ተሳሉ።

17እግዚአብሔር ግን ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀ፤ ዮናስም በዓሣው ሆድ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ዐደረ።