ዮሐንስ 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዮሐንስ 14:1-31

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን አበረታታ

1“ልባችሁ አይጨነቅ፤ በእግዚአብሔር እመኑ14፥1 ወይም እናንተ በእግዚአብሔር ታምናላችሁ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ ይህ ባይሆንማ ኖሮ እነግራችሁ ነበር፤ የምሄደውም ስፍራ ላዘጋጅላችሁ ነው። 3ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ። 4እኔ ወደምሄድበትም ስፍራ የሚያደርሰውን መንገድ ታውቃላችሁ።”

ወደ አብ የሚያደርሰው መንገድ

5ቶማስም፣ “ጌታ ሆይ፤ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም፤ ታዲያ፣ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” አለው።

6ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7እኔን ብታውቁኝ ኖሮ አባቴንም ባወቃችሁት ነበር።14፥7 አንዳንድ የጥንት ቅጆች በርግጥ እኔን ብታውቁ አባቴንም ታውቃላችሁ ይላሉ። ከአሁን ጀምሮ ግን ታውቁታላችሁ፤ አይታችሁታልም።”

8ፊልጶስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው።

9ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “አንተ ፊልጶስ! ይህን ያህል ጊዜ ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቷል፤ እንዴትስ፣ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10እኔ በአብ እንዳለሁ፣ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? የምነግራችሁ ቃል ከራሴ አይደለም፤ ነገር ግን ሥራውን የሚሠራው በእኔ የሚኖረው አብ ነው። 11እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ ስነግራችሁ እመኑኝ፤ ሌላው ቢቀር ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንኳ እመኑ። 12እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም የሚበልጥ ያደርጋል። 13አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ 14ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ እኔ አደርገዋለሁ።

ስለ መንፈስ ቅዱስ የተሰጠ ተስፋ

15“ብትወድዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ። 16እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17እርሱም የእውነት መንፈስ ነው፤ ዓለም ስለማያየውና ስለማያውቀው ሊቀበለው አይችልም። እናንተ ግን፣ አብሯችሁ ስለሚኖርና በውስጣችሁ ስለሚሆን14፥17 አንዳንድ የጥንት ቅጆች በውስጣችሁ ስላለ ይላሉ። ታውቁታላችሁ። 18ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ። እኔ ሕያው ስለሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20እኔ በአባቴ እንዳለሁ፣ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፣ እኔም ደግሞ በእናንተ እንዳለሁ በዚያ ቀን ትረዳላችሁ። 21የሚወድደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወድደኝንም አባቴ ይወድደዋል፤ እኔም እወድደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”

22ከዚያም የአስቆሮቱ ያልሆነው ይሁዳ፣ “ጌታ ሆይ፤ ታዲያ፣ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ የምትገልጠው እንዴት ነው?” አለው።

23ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “የሚወድደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወድደዋል፤ ወደ እርሱ እንመጣለን፤ ከእርሱም ጋር እንኖራለን። 24የማይወድደኝ ቃሌን አይጠብቅም። ይህ የምትሰሙት ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።

25“አሁን ከእናንተ ጋር እያለሁ ይህን ሁሉ ነግሬአችኋለሁ፤ 26አብ በስሜ የሚልከው አጽናኙ መንፈስ ቅዱስ ግን ሁሉን ነገር ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል። 27ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም።

28“ ‘እሄዳለሁ፤ ተመልሼም ወደ እናንተ እመጣለሁ’ ማለቴን ሰምታችኋል፤ ብትወድዱኝስ አብ ከእኔ ስለሚበልጥ ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር፤ 29የተናገርሁት ሲፈጸም እንድታምኑ፣ ከመሆኑ በፊት አሁን ነግሬአችኋለሁ። 30የዚህ ዓለም ገዥ ስለሚመጣ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም። እርሱም በእኔ ላይ ሥልጣን የለውም፤ 31ነገር ግን እኔ አብን እንደምወድድ፣ አባቴ ያዘዘኝንም እንደማደርግ ዓለም እንዲያውቅ ነው።

“ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።