ዘፍጥረት 12 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘፍጥረት 12:1-20

የአብራም መጠራት

1እግዚአብሔር (ያህዌ) አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን፣ ወገንህንና የአባትህን ቤት ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።

2“ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤

ደግሞም እባርክሃለሁ፤

ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤

ለሌሎች በረከት ትሆናለህ።

3የሚባርኩህን እባርካለሁ፤

የሚረግሙህን እረግማለሁ፤

በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣

በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።”

4ስለዚህ አብራም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም አብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ሲወጣ ዕድሜው 75 ዓመት ነበረ። 5አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ሳሉ ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዘው በመጓዝ ከነዓን ምድር ገቡ።

6አብራም ትልቁ የሞሬ ዛፍ እስከሚገኝበት እስከ ሴኬም ድረስ በምድሪቱ ዘልቆ ሄደ። በዚያን ጊዜ ከነዓናውያን በዚሁ ምድር ይኖሩ ነበር። 7እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት አምላክ (ያህዌ) በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ።

8ከዚያም ተነሥቶ ከቤቴል በስተ ምሥራቅ ወዳሉት ተራሮች ሄደ፤ ቤቴልን በምዕራብ፣ ጋይን በምሥራቅ አድርጎ ድንኳን ተከለ፣ በዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ጠርቶ ጸለየ። 9አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።

አብራም በግብፅ አገር

12፥10-20 ተጓ ምብ – ዘፍ 20፥1-1826፥1-11

10በዚያም ምድር ጽኑ ራብ ገብቶ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አብራም ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ ግብፅ ወረደ። 11ግብፅ ለመግባት ጥቂት ሲቀረው አብራም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ውብ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ 12ግብፃውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ፣ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ብለው እኔን ይገድላሉ፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13ስለዚህ ለአንቺ ሲሉ እንዲንከባከቡኝ፣ ሕይወቴም እንድትተርፍ፣ ‘እኅቱ ነኝ’ በዪ።”

14አብራም በግብፅ አገር እንደ ደረሰ ግብፃውያን፣ ሦራ እጅግ ውብ ሴት እንደ ሆነች አዩ፤ 15የፈርዖንም ሹማምት ባዩአት ጊዜ፣ ለፈርዖን አድንቀው ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ወሰዷት። 16በእርሷም ምክንያት ፈርዖን አብራምን አክብሮ አስተናገደው፤ በጎችና ከብቶች፣ ተባዕትና እንስት አህዮች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችን ሰጠው።

17እግዚአብሔርም (ያህዌ) በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተ ሰዎቹን በጽኑ ደዌ መታቸው። 18ከዚያም ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ‘ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርኸኝም?’ 19ለምን ‘እኅቴ ናት’ አልኸኝ? ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል አሁንም ሚስትህ ይህችው፤ ይዘሃት ሂድ!” 20ከዚያም ፈርዖን ስለ አብራም ለባለሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋር አሰናበቱት።