ዘፀአት 18 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘፀአት 18:1-27

ዮቶር ወደ ሙሴ መጣ

1የምድያም ካህን የሙሴ ዐማት ዮቶር፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገላቸውን ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር (ያህዌ) እስራኤልን ከግብፅ እንዴት እንዳወጣቸው ሰማ።

2ሙሴ ሚስቱን ሲፓራን ከመለሳት በኋላ ዐማቱ ዮቶር እርሷንና ሁለት ወንድ ልጆቿን ተቀብሏቸው ነበር። 3ሙሴ፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ለማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ጌርሳም18፥3 በዕብራይስጥ ጌርሳም የሚለው የቃል ድምፅ፣ መጻተኛ በዚያ አለ ከሚለው ሐረግ ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው። አለው። 4“የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ከፈርዖን ሰይፍ አድኖኛልና” ለማለት ደግሞ ሁለተኛውን ልጁን አልዓዛር18፥4 አልዓዛር ማለት፣ አምላኬ ረዳት ነው ማለት ነው። አለው።

5የሙሴ ዐማት ዮቶር ከሙሴ ወንድ ልጆችና ሚስት ጋር ሆኖ በምድረ በዳ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አጠገብ ወደ ሰፈረበት ወደ ሙሴ መጣ። 6ዮቶር፣ “እኔ ዐማትህ ዮቶር፣ ከሚስትህና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋር እየመጣን ነው” ሲል መልእክት ላከበት። 7ስለዚህ ሙሴ ዐማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ። 8ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዴት እንዳዳናቸው ለዐማቱ ነገረው። 9ዮቶርም እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን ከግብፃውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ። 10እንዲህም አለ፤ “ከግብፃውያን እጅና ከፈርዖን ለታደጋችሁ፣ ከግብፃውያን እጅ ሕዝቡን ለታደገ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ምስጋና ይሁን”። 11እግዚአብሔር (ያህዌ) ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጓልና።” 12ከዚያም የሙሴ ዐማት ዮቶር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌሎች መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም) አቀረበ፤ አሮንም ከሙሴ ዐማት ጋር በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት እንጀራ ለመብላት ከእስራኤል አለቆች ሁሉ ጋር መጣ።

13በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን ለመዳኘት ተቀመጠ፤ እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ። 14ዐማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው።

15ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ። 16ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጕዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።”

17የሙሴ ዐማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም። 18አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም። 19ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን አድምጠኝ፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአንተ ጋር ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት (የሕዝብ ተወካይ መሆን አለብህ)፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ። 20ሥርዐቶቹንና ሕጎቹን አስተምራቸው፤ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሚገባቸው አሳያቸው። 21ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺሕ፣ የመቶ፣ የአምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው። 22በማንኛውም ጊዜ ሕዝቡን ይዳኙ፤ ቀላሉን ነገር እነርሱ ይወስኑ፤ አስቸጋሪ የሆነውን ጕዳይ ሁሉ ግን ለአንተ እንዲያቀርቡ አድርግ፤ ሥራውን ስለሚያግዙህ ሸክምህ ይቃለላል። 23አንተ ይህን ብታደርግና እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህንኑ ቢያዝህ፣ ድካምህን መቋቋም ትችላለህ፤ እነዚህም ሰዎች ሁሉ ረክተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።”

24ሙሴ ዐማቱን ሰማ፤ ያለውንም ሁሉ ፈጸመ። 25ከእስራኤል መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠና፤ የሕዝብ መሪዎች፣ በሺዎች፣ በመቶዎች፣ በአምሳዎች በዐሥሮች ላይም አለቆች አደረጋቸው። 26ሁልጊዜም የሕዝብ ዳኞች ሆነው አገለገሉ፤ አስቸጋሪ ጕዳዮችን ወደ ሙሴ አመጡ፤ ቀላል የሆነውን ራሳቸው ወሰኑ። 27ከዚያም ሙሴ ዐማቱን በጕዞው ሸኘው፤ ዮቶርም ወደ አገሩ ተመለሰ።