ዘዳግም 14 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ዘዳግም 14:1-29

ንጹሕና ንጹሕ ያልሆነ ምግብ

14፥3-20 ተጓ ምብ – ዘሌ 11፥1-23

1እናንተ የአምላካችሁ የእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ልጆች ናችሁ፤ ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትቦጭቁ፤ ከግንባራችሁ በላይ ያለውን ጠጕር አትላጩ፤ 2ምክንያቱም አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ነህ፤ ለራሱ የተለየ ሕዝብ እንድትሆንለት እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድር ላይ ከሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ አንተን መርጦሃል።

3ማናቸውንም ርኩስ ነገር አትብላ። 4የምትበሏቸው እንስሳት እነዚህ ናቸው፤ በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ 5ዋላ፣ ድኵላ፣ ሰስ፣ የበረሓ ፍየል፣ ዋሊያ፣ ሚዳቋ፣ አጋዘን14፥5 በዚህ ስፍራ የተጠቀሱት አንዳንድ አዕዋፍና እንስሳት ማንነታቸው በትክክል አይታወቅም።6ሰኰናው ስንጥቅ የሆነውን፣ ለሁለት የተከፈለውንና የሚያመሰኳ ማናቸውንም እንስሳ ብላ። 7ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እንስሳት መካከል ግመልን፣ ጥንቸልንና ሽኮኮን አትብሉ፤ እነርሱ ቢያመሰኩ እንኳ፣ ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ባለመሆኑ፣ በሥርዐቱ መሠረት በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 8ዐሳማም እንደዚሁ ርኩስ ነው፤ ምንም እንኳ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም፣ ስለማያመሰኳ፣ እርሱ ለእናንተ ንጹሕ አይደለም፤ የእነዚህን ሥጋ አትብሉ፤ ጥምባቸውንም አትንኩ።

9በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ፍጡራን ሁሉ ክንፍና ግልፋፊ ያለውን ማናቸውንም ብሉ፤ 10ክንፍና ግልፋፊ የሌለውን ግን አትብሉ፤ ለእናንተ ርኩስ ነው።

11ንጹሕ የሆነውን ወፍ ሁሉ መብላት ትችላላችሁ። 12የሚከተሉትን ግን አትበሉም፤ እነርሱም፦ ንስር፣ ገዴ፣ ዓሣ አውጪ፣ 13ጭልፊት፣ ጭላት፣ ማናቸውም ዐይነት ዐድኖ በል አሞራ፣ 14ማናቸውም ዐይነት ቍራ፣ 15ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማናቸውም ዐይነት በቋል፣ 16ጕጕት፣ ጋጋኖ፣ የውሃ ዶሮ፣ 17ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣ እርኩም፣ 18ሽመላ፣ ማናቸውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጅንጅላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ ናቸው።

19ክንፍ ያላቸው ጥቃቅን ነፍሳት ሁሉ ለእናንተ ርኩስ ናቸው፤ እነርሱን አትብሏቸው። 20ንጹሕ የሆነውን ማናቸውንም ክንፍ ያለውን ፍጡር ግን ብሉ።

21አንተ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ቅዱስ ሕዝብ ነህና የሞተውን ሁሉ አትብላ፤ ከከተሞችህ በአንዲቱ ለሚኖር መጻተኛ ስጠው፤ ይብላውም፤ ለውጭ አገር ሰው ሽጠው። የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።

ዐሥራት

22በየዓመቱ ከዕርሻህ ከምታገኘው ምርት ከዐሥር አንዱን እጅ ለይተህ አስቀምጥ። 23ምንጊዜም አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ማክበር ትማር ዘንድ፣ የአዲሱን ወይን ጠጅህንና የዘይትህን ዐሥራት፣ የቀንድ ከብትህን፣ የበግና የፍየል መንጋህን በኵራት ስሙ እንዲጠራበት በሚመርጠው ስፍራ፣ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ብላ። 24ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ባርኮህ ሳለ፣ መንገዱ ቢርቅብህና እግዚአብሔር (ያህዌ) የስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ የሚመርጠው ስፍራ ከአንተ እጅግ ከመራቁ የተነሣ ዐሥራትህን ወደዚያ ቦታ ማድረስ ካልቻልህ፣ 25ዐሥራትህን በብር ለውጥ፤ ብሩንም ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ወደሚመርጠው ስፍራ ሂድ። 26በብሩም ደስ ያለህን ሁሉ፣ ማለትም የቀንድ ከብት፣ በግ፣ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ብርቱ መጠጥ ወይም የምትሻውን ሁሉ ግዛበት። ከዚያም አንተና ቤተ ሰብህ በአምላክህ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት በዚያ ትበላላችሁ፤ ሐሤትም ታደርጋላችሁ። 27የራሱ ድርሻ ወይም ርስት ስለሌለው፣ በከተሞችህ የሚኖረውን ሌዋዊ ቸል አትበለው።

28በየሦስት ዓመቱ መጨረሻ የዚያን ዓመት ሰብል ዐሥራት በሙሉ አውጥተህ በከተሞችህ ውስጥ አከማች። 29ይህን የምታደርገው የራሱ ድርሻ ወይም ርስት የሌለው ሌዋዊና መጻተኛ፣ በከተሞችህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች መጥተው እንዲበሉና እንዲጠግቡ፣ አንተንም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጆችህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ ነው።