ኢዮብ 30 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዮብ 30:1-31

1“አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፣

ከመንጋዬ ጠባቂ ውሾች ጋር እንዳይቀመጡ፣

አባቶቻቸውን የናቅኋቸው፣

እነዚህ ይሣለቁብኛል።

2ጕልበት የከዳቸው፣

የክንዳቸው ብርታት ምን ፋይዳ ይሞላልኝ ነበር?

3ከችጋርና ከራብ የተነሣ ጠወለጉ፤

ሰው በማይኖርበት በረሓ፣

በደረቅም ምድር በሌሊት ተንከራተቱ።30፥3 ወይም ተሠቃዩ

4ከቍጥቋጦ ምድር ጨው ጨው የሚል አትክልት ለቀሙ፤

ምግባቸውም የክትክታ ሥር ነበር።

5ከኅብረተ ሰቡ ተለይተው ተባረሩ፤

ሰዎች እንደ ሌባ ይጮኹባቸዋል።

6በዐለት መካከል በምድር ጕድጓድ፣

በደረቅ ሸለቆ ዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገደዱ።

7በጫካ ውስጥ ያናፋሉ፤

በእሾኻማ ቍጥቋጦ መካከልም ይታፈጋሉ።

8ስማቸው የማይታወቅ አልባሌ ናቸው፤

ከምድሪቱም ተባርረዋል።

9“አሁን ግን ልጆቻቸው በዘፈን ይሣለቁብኛል፤

በእነርሱም ዘንድ መተረቻ ሆኛለሁ።

10ይጸየፉኛል፣ ወደ እኔም አይቀርቡም፤

ያለ ምንም ይሉኝታ በፊቴ ይተፋሉ።

11እግዚአብሔር የቀስቴን አውታር ስላላላውና በመከራም ስለ መታኝ፣

በፊቴ መቈጠብን ትተዋል።

12በቀኜ በኩል ባለጌዎች30፥12 በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም በትክክል አይታወቅም። ሆ! ብለው ተነሡብኝ፤

ለእግሬም ወጥመድ ዘረጉ፤

የዐፈር ድልድልም አዘጋጁብኝ።

13መንገድ ዘጉብኝ፤

የሚገታቸው30፥13 ወይም ማንም ሊረዳው አይችልም አሉ። ሳይኖር፣

ሊያጠፉኝ ተነሡ።

14በሰፊ ንቃቃት ውስጥ እንደሚመጣ ሰው መጡብኝ፤

በፍርስራሽም መካከል እየተንከባለሉ ደረሱብኝ።

15በድንጋጤ ተውጫለሁ፤

ክብሬ በነፋስ እንደሚወሰድ ተወስዷል፤

በሰላም መኖሬም እንደ ደመና እልም ብሎ ጠፍቷል።

16“አሁን ነፍሴ በውስጤ ዐለቀች፤

የመከራ ዘመንም ይዞኛል።

17ደዌ በሌሊት ዐጥንቴን ይበሳል፤

የሚቈረጥመኝም ፋታ አይሰጠኝም።

18እግዚአብሔር በታላቅ ኀይሉ ልብሴን30፥18 የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን፣ እንደ ልብስ ሆኖብኛል ይላል። ጨምድዷል፤

በልብሴም ክሳድ ዐንቆ ይዞኛል።

19እርሱ ጭቃ ውስጥ ጥሎኛል፤

እኔም ከዐፈርና ከዐመድ አልተሻልሁም።

20“እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ነገር ግን አልመለስህልኝም፤

በፊትህም ቆምሁ፤ አንተ ግን ዝም አልኸኝ።

21ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤

በክንድህም ብርታት አስጨነቅኸኝ።

22ወደ ላይ ነጥቀህ በነፋስ ፊት አበረርኸኝ፤

በዐውሎ ነፋስም ወዲያ ወዲህ ወዘወዝኸኝ።

23ለሕያዋን ሁሉ ወደ ተመደበው ስፍራ፣

ወደ ሞት እንደምታወርደኝ ዐውቃለሁ።

24“የተጐዳ ሰው ተጨንቆ ድረሱልኝ ብሎ ሲጮኽ፣

በርግጥ ክንዱን የሚያነሣበት ማንም የለም።

25በመከራ ውስጥ ላሉት አላለቀስሁምን?

ለድኾችስ ነፍሴ አላዘነችምን?

26ነገር ግን መልካም ስጠብቅ፣ ክፉ ነገር ደረሰብኝ፤

ብርሃንንም ስጠባበቅ፣ ጨለማ መጣብኝ።

27በውስጤ ያለው ነውጥ አላቋረጠም፤

የመከራ ዘመንም መጣብኝ።

28በፀሓይ አይደለም እንጂ፣ ጠቋቍሬ እዞራለሁ፤

በጉባኤ መካከል ቆሜ ለርዳታ እጮኻለሁ።

29የቀበሮች ወንድም፣

የጕጕቶችም ባልንጀራ ሆኛለሁ።

30ቈዳዬ ጠቍሮ ተቀረፈ፤

ዐጥንቴም በትኵሳት ነደደ።

31በገናዬ ለሐዘን፣

እንቢልታዬም ለልቅሶ ተቃኝቷል።