ኢያሱ 8 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢያሱ 8:1-35

የጋይ ከተማ ተደመሰሰ

1ከዚያም እግዚአብሔር ኢያሱን እንዲህ አለው፤ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ሰራዊቱን ሁሉ ይዘህ በመውጣት ጋይን ውጋ፤ የጋይን ንጉሥ፣ ሕዝቡን፣ ከተማውንና ምድሩን አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼሃለሁና። 2በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ያደረግኸውንም ሁሉ፣ በጋይና በንጉሥዋ ላይ ትደግመዋለህ፤ በዚህ ጊዜ ግን ምርኮውንና ከብቱን ለራሳችሁ ታደርጉታላችሁ፤ ታዲያ ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ የደፈጣ ጦር አዘጋጅ።”

3ስለዚህ ኢያሱና ሰራዊቱ በሙሉ ጋይን ለመውጋት ወጡ፤ ኢያሱም ምርጥ ከሆኑት ተዋጊዎቹ ሠላሳ ሺሕ ጦር አዘጋጅቶ በሌሊት ላካቸው፤ 4እንዲህ የሚል ትእዛዝም ሰጣቸው፤ “እነሆ፤ ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ ታደፍጣላችሁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ነቅታችሁ ተጠባበቁ፤ 5እኔና አብረውኝ ያሉት ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንጠጋለን፤ ሰዎቹ ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሊወጉን ወደኛ ሲመጡ፤ እኛ ደግሞ እንሸሻለን፤ 6እነርሱም፣ ‘ከዚህ ቀደም እንዳደረጉት አሁንም ከእኛ በመሸሽ ላይ ናቸው’ በማለት ከከተማዪቱ እስክናርቃቸው ድረስ ይከታተሉናል፤ በዚህ ሁኔታ እኛም እንሸሻለን፤ 7እናንተም ከተደበቃችሁበት ትወጡና ከተማዪቱን ትይዛላችሁ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ከተማዪቱን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋልና። 8ከተማዪቱን ስትይዙም በእሳት አቃጥሏት፤ እግዚአብሔር ያዘዘውንም አድርጉ፤ እነሆ አዝዣችኋለሁ።”

9ከዚያም ኢያሱ ሰዎቹን ላካቸው፤ እነርሱም ሄደው ከጋይ በስተ ምዕራብ በቤቴልና በጋይ መካከል ባለው ቦታ አደፈጡ፤ ኢያሱ ግን እዚያው ከሕዝቡ ጋር ዐደረ።

10በማግስቱም ጧት ኢያሱ ማልዶ በመነሣት ወንዶቹን ሰበሰበ፤ እርሱና የእስራኤል አለቆችም ከፊት ሆነው እየመሯቸው ወደ ጋይ ወጡ። 11ከእርሱ ጋር የነበሩትም ተዋጊዎች በሙሉ ወጥተው ወደ ከተማዪቱ በመጠጋት ከፊት ለፊቷ ደረሱ፤ ከዚያም ከጋይ በስተ ሰሜን መካከል ካለው ሸለቆ ማዶ ሰፈሩ። 12ኢያሱ ቀደም ብሎ አምስት ሺሕ ሰው ያህል በመውሰድ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ፣ በቤቴልና በጋይ መካከል እንዲያደፍጡ አድርጎ ነበር። 13ከከተማዪቱ በስተ ሰሜን የነበሩትንም፣ ከከተማዪቱ በስተ ምዕራብ የሸመቁትንም ወታደሮች ሁሉ ስፍራ ስፍራቸውን እንዲይዙ አደረጋቸው፤ በዚያችም ሌሊት ኢያሱ ወደ ሸለቆው ሄደ።

14የጋይ ንጉሥ ይህን ባየ ጊዜ እርሱና የከተማዪቱ ወንዶች ሁሉ ማልደው በመገሥገሥ፣ እስራኤልን ለመውጋት ከዓረባ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ስፍራ መጡ፤ ንጉሡ ግን ከከተማዪቱ በስተ ጀርባ ያደፈጠ ኀይል የሚጠባበቀው መሆኑን አያውቅም ነበር። 15ኢያሱና እስራኤል በሙሉ ድል የተመቱ መስለው በመታየት፣ ወደ ምድረ በዳው ሸሹ። 16የጋይ ሰዎች በሙሉ እንዲያሳድዷቸው ተጠሩ፤ ኢያሱንም አሳደዱት፤ በዚህ ሁኔታም የጋይ ሰዎች ከከተማዪቱ እንዲርቁ ተደረገ። 17እስራኤልን ለማሳደድ ከጋይና ከቤቴል ያልወጣ ወንድ አልነበረም፤ ከተማዪቱንም ከፍተው ትተው እስራኤልን ማሳደድ ያዙ።

18እግዚአብሔርም ኢያሱን፣ “ከተማዪቱን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፣ የያዝኸውን ጦር ወደ ጋይ አነጣጥር” አለው፤ ኢያሱም ጦሩን ወደ ጋይ አነጣጠረ። 19ይህን እንዳደረገም ያደፈጡት ሰዎች ከተደበቁበት ስፍራ በፍጥነት ወጥተው ወደ ፊት ሮጡ፤ ገብተው ከተማዪቱን ያዟት፤ ወዲያውኑም በእሳት አቃጠሏት።

20የጋይ ሰዎች ወደ ኋላ ዞረው ሲመለከቱ የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሸሹ የነበሩት እስራኤላውያን ፊታቸውን ስላዞሩባቸውም፣ በየትኛውም በኩል ማምለጫ መንገድ አልነበራቸውም። 21ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ያደፈጠው ጦር ከተማዪቱን መያዙንና ጢሱ ወደ ላይ መውጣቱን ሲያዩ፣ ወደ ኋላ ተመልሰው በጋይ ሰዎች ላይ ዐደጋ ጣሉባቸው፤ 22ያደፈጡትም ሰዎች እንደዚሁ ከከተማዪቱ ወጥተው መጡባቸው። ስለዚህ እስራኤላውያን በዚያም በዚህም ስለ ከበቧቸው የጋይን ሰዎች ከመካከል አደረጓቸው፤ እስራኤላውያንም ሰዎቹን ፈጇቸው፤ አንድ እንኳ የተረፈ ወይም ያመለጠ አልነበረም፤ 23ነገር ግን የጋይን ንጉሥ ከነሕይወቱ ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።

24እስራኤላውያን የጋይን ወንዶች ሁሉ ባሳደዷቸው ሜዳና ምደረ በዳ ከጨረሷቸውና እያንዳንዳቸውንም በሰይፍ ከፈጁ በኋላ፣ ወደ ከተማዪቱ ተመልሰው በዚያ ያገኙትን ሁሉ ገደሉ። 25በዚያች ዕለት የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐለቁ፤ የወንዶቹና የሴቶቹም ብዛት ዐሥራ ሁለት ሺሕ ነበር። 26ኢያሱ በጋይ የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ ፈጽሞ እስኪያጠፋቸው8፥26 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው። ድረስ ጦር ያነጣጠረባትን እጁን አላጠፈም ነበር። 27እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ኢያሱን ባዘዘው መሠረት፣ በከተማዪቱ ያገኙትን እንስሳትና ምርኮ ብቻ ለራሳቸው አደረጉ።

28ስለዚህ ኢያሱ ጋይን አቃጠላት፤ እስከ ዛሬ እንደሚታየውም ለዘላለም የዐመድ ቍልልና ባድማ አደረጋት። 29የጋይንም ንጉሥ በዛፍ ላይ ሰቀለው፤ ሬሳውንም እስኪመሽ ድረስ እዚያው እንዳለ ተወው፤ ፀሓይ ስትጠልቅም፣ ኢያሱ ሬሳውን እንዲያወርዱትና በከተማው በር ላይ እንዲጥሉት አዘዘ፤ የትልልቅ ድንጋይ ቍልልም ከመሩበት፤ ይህም እስከ ዛሬ ድረስ እዚያው ይገኛል።

ቃል ኪዳኑ በጌባል ተራራ ታደሰ

30ከዚያም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። 31መሠዊያውንም የሠራው የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ፣ እስራኤላውያንን ባዘዛቸው መሠረት ሲሆን፣ ይህንም የሠራው በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ባልተጠረበና የብረት መሣሪያ ባልነካው ድንጋይ ነው፤ በዚህም ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ የኅብረት መሥዋዕትም8፥31 በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል። ሠዉ። 32ኢያሱም ሙሴ የጻፈውን የሕግ መጽሐፍ እስራኤላውያን እያዩ በድንጋዮች ላይ ቀረጸው። 33እስራኤል በሙሉ መጻተኛውም ሆነ ተወላጁ፣ ሽማግሌዎቻቸውም ሆኑ ሹማምታቸው እንዲሁም ዳኞቻቸው የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ተሸከሙት ሌዋውያን ካህናት ፊታቸውን አዙረው፣ በታቦቱ ግራና ቀኝ ቆመው ነበር። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እንዲባርኩ መመሪያ በሰጠ ጊዜ፣ አስቀድሞ ባዘዘው መሠረት፣ ግማሹ ሕዝብ በገሪዛን ተራራ፣ ግማሹ ደግሞ በጌባል ተራራ ፊት ለፊት ቆመ።

34ከዚህ በኋላ ኢያሱ፣ የሕጉን ቃላት በሙሉ ማለትም በረከቱንና መርገሙን ሁሉ፣ ልክ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው አነበበ። 35ኢያሱ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ሴቶች፣ ሕፃናትና በመካከላቸው የኖሩ መጻተኞች ባሉበት ያነበበው፣ አንድም ሳይቀር ሙሴ ያዘዘውን ቃል ሙሉ በሙሉ ነበር።