ኢያሱ 13 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢያሱ 13:1-33

ወደ ፊት የሚያዝ ምድር

1ኢያሱ በሸመገለና ዕድሜው በገፋ ጊዜ፣ እግዚአብሔር እንዲህ አለው፤ “እነሆ አርጅተሃል፤ ዕድሜህም ገፍቷል፤ ነገር ግን መያዝ ያለበት እጅግ በጣም ሰፊ ምድር ገና አለ።

2“የሚቀረውም ምድር ይህ ነው፤

“እርሱም የፍልስጥኤማውያንና የጌሹራውያን አገር ሁሉ ነው፤ 3ከግብፅ በስተ ምሥራቅ ከሚገኘው ከሺሖር ወንዝ አንሥቶ፣ በሰሜን እስከ አቃሮን ወሰን ያለው አገር፣ ሁሉም እንደ ከነዓናውያን ምድር ይቈጠራል። ይኸውም በጋዛ፣ በአሽዶድ፣ በአስቀሎና፣ በጌትና በአቃሮን የሚኖሩትን የአምስቱን የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምድር የሚያካትት ሲሆን፣

ይህም የኤዋውያን ምድር ነበር። 4በደቡብ በኩል፤

የከነዓናውያን ምድር ሁሉና የሲዶናውያን ይዞታ ከሆነችው ከመዓራ አንሥቶ እስከ አፌቅ ያለው የአሞራውያን ግዛት፣

5የጌባላውያንም ምድር13፥5 የቢብሎስ አካባቢ ነው።

በምሥራቅም ከበኣልጋድ አንሥቶ በአርሞንዔም ተራራ ግርጌ ዐልፎ፣ እስከ ሐማት መተላለፊያ13፥5 ወይም፣ “እስከ ሌቦ ሐማት” ያለው የሊባኖስ ምድር ሁሉ ነው።

6“ከሊባኖስ እስከ ማሴሮን ባለው ተራራማ ምድር ላይ የሚኖሩትን ሁሉ፣ ሲዶናውያንንም ጭምር እኔው ራሴ ከእስራኤላውያን ፊት አሳድጄ አስወጣቸዋለሁ። ብቻ አንተ ባዘዝሁህ መሠረት ምድሪቱን ርስት አድርገህ ለእስራኤላውያን አካፍል። 7ይህንም ለዘጠኙ ነገድና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገህ አካፍል።”

ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለው ምድር አከፋፈል

8ሌላው የምናሴ ነገድ እኩሌታ፣ የሮቤል ነገድና የጋድ ነገድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ እንደየድርሻቸው ከፋፍሎ በመደበላቸው መሠረት፣ ራሱ ሙሴ የሰጣቸውን ርስት ተቀበሉ።

9ይህም ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና በሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ እስከ ዲቦን የሚደርሰውን የሜድባን ደጋማ ምድር በሙሉ ይይዛል፤ 10እንዲሁም በሐሴቦን ተቀምጦ እስከ አሞናውያን ዳርቻ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል።

11በተጨማሪም ገለዓድን፣ የጌሹራውያንንና የማዕካታውያንን ግዛት ሁሉ፣ የአርሞንዔምን ተራራ በሙሉ፣ ባሳንንም ሁሉ እስከ ሰልካ ድረስ ይይዛል። 12ይህም በአስታሮትና በኤድራይ ሆኖ የገዛውን በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት በሙሉ ያጠቃልላል፤ ዐግም በሕይወት ከቀሩት ከመጨረሻዎቹ ከራፋይም ዘሮች አንዱ ነበር። እነዚህንም ሙሴ ድል አደረጋቸው፤ ምድራቸውንም ያዘ፤ 13ነገር ግን እስራኤላውያን የጌሹርንና የማዕካትን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላቸው ይኖራሉ።

14ለሌዊ ነገድ ግን ርስት አልሰጠም፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበው ቍርባን በተሰጣቸው ተስፋ መሠረት ርስታቸው ነውና።

15ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለሮቤል ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

16ድንበራቸው ከአርኖን ሸለቆ ዳርቻ ካለው ከአሮዔርና ከሸለቆው መካከል ካለችው ከተማ አንሥቶ ያለው ግዛት ሲሆን፣ ሜድባ አጠገብ ያለውን ደጋውን አገር በሙሉ፣ 17ሐሴቦንና በደጋው ላይ ያሉትን ከተሞቿን በሙሉ፣ እንዲሁም ዲቦንን፣ ባሞትባኣልን፣ ቤትበኣልምዖን፣ 18ያሀጽን፣ ቅዴሞትን፣ ሜፍዓትን፣ 19ቂርያታያምን፣ ሴባማን፣ በሸለቆው ኰረብታ ላይ ያለችውን ጼሬትሻሐርን፣ 20ቤተፌጎርን፣ የፈስጋን ሸንተረሮችና ቤትየሺሞትን፣ 21ማለት በደጋው አገር የሚገኙት ከተሞች ሁሉና መቀመጫውን በሐሴቦን አድርጎ የገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት በሙሉ ያካትታል። ሙሴ ሴዎንንና በዚያው ምድር ተቀማጭ የነበሩትን መሳፍንት፤ አዊ፣ ሮቆም፣ ሱር፣ ሑርና ሪባ የተባሉትን የምድያም አለቆች ድል አደረጋቸው። 22በጦር ሜዳ ከሞቱት ሌላ እስራኤላውያን የቢዖርን ልጅ ምዋርተኛውን በለዓምን በሰይፍ መትተው ገደሉት።

23የሮቤል ነገድ ወሰን የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። የሮቤል ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ፤

24ሙሴ በየጐሣቸው መድቦ ለጋድ ነገድ የሰጠው ርስት ይህ ነው፤

25ድንበራቸው ኢያዜር፣ የገለዓድን ከተሞች በሙሉ በረባት አጠገብ እስካለው እስከ አሮዔር የሚደርሰውን የአሞናውያን አገር እኩሌታ፣ 26ከሐሴቦን እስከ ራማት ምጽጴና ከዚያም እስከ ብጦኒም፣ ከመሃናይም እስከ ደቤር ግዛት ያለውን፣ 27በሸለቆው ውስጥ ደግሞ ቤትሀራምን፣ ቤትኒምራን፣ ሱኮትን፣ ዳፎንንና እስከ ኪኔሬት13፥27 የገሊላ ባሕር ነው። ባሕር ጫፍ የሚደርሰውን ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ቀሪውን የሐሴቦን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት ያካትታል።

28የጋድ ነገድ በየጐሣቸው የወረሷቸው ከተሞችና መንደሮቻቸው እነዚህ ነበሩ።

29ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ማለት ለገሚሱ የምናሴ ቤተ ሰብ ዘሮች በየጐሣቸው የሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤

30ድንበራቸው ከመሃናይም አንሥቶ ባሳንን በሙሉ ይጨምርና፣ በባሳን ያሉትን ስድሳ የኢያዕር ከተሞች ሁሉ ይዞ የባሳን ንጉሥ የዐግን ግዛት ሁሉ የሚያካትት ሲሆን፣ 31የገለዓድን እኩሌታ፣ በባሳን የዐግ መንግሥት ዋና ከተማ የሆኑትን አስታሮትንና ኤድራይን ይጨምራል።

እነዚህ ለምናሴ ልጅ ለማኪር ዘሮች የተሰጡ ሲሆን፣ ይህም ለግማሾቹ የማኪር ልጆች በየጐሣቸው የተሰጡ ናቸው።

32ሙሴ ከኢያሪኮ በስተ ምሥራቅ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ሜዳ ሳለ የሰጣቸው ርስት ይህ ነበር። 33ለሌዊ ነገድ ግን ሙሴ ርስት አልሰጠም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው እርሱ ራሱ ርስታቸው ነውና።