ኢዩኤል 1 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢዩኤል 1:1-20

1ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤

የአንበጣ ወረራ

2እናንት ሽማግሌዎች፣ ይህን ስሙ፤

በምድሪቱም የምትኖሩ ሁላችሁ፣ አድምጡ፤

በእናንተ ዘመንም ሆነ በአባቶቻችሁ ዘመን፣

እንዲህ ዐይነት ነገር ሆኖ ያውቃልን?

3ይህን ለልጆቻችሁ ተናገሩ፤

ልጆቻችሁ ለልጆቻቸው ይንገሩ፤

ልጆቻቸውም ለሚቀጥለው ትውልድ ይንገሩ።

4ከአንበጣ መንጋ1፥4 በዚህ ክፍል፣ ስለ አንበጦች የሚገልጹት አራት የዕብራይስጥ ቃላት፣ ትክክለኛ ትርጕም አይታወቅም። የተረፈውን፣

ትልልቁ አንበጣ በላው፤

ከትልልቁ አንበጣ የተረፈውን፣

ኵብኵባ በላው፤

ከኵብኵባ የተረፈውን፣

ሌሎች አንበጦች በሉት።

5እናንት ሰካራሞች፤ ተነሡ፤ አልቅሱ፤

እናንት የወይን ጠጅ ጠጪዎች ሁሉ፤ ዋይ በሉ፤

ስለ አዲሱ የወይን ጠጅ ዋይ ብላችሁ አልቅሱ፤

አፋችሁ ላይ እንዳለ ተነጥቃችኋልና።

6ኀያልና ቍጥር ስፍር የሌለው ሕዝብ፣

ምድሬን ወሯታልና፤

ጥርሱ እንደ አንበሳ ጥርስ፣

መንጋጋውም እንደ እንስት አንበሳ መንጋጋ ነው።

7የወይን ቦታዬን ባድማ አደረገው፤

የበለስ ዛፎቼንም ቈራረጠ፤

ቅርንጫፎቻቸው ነጭ ሆነው እስኪታዩ ድረስ፣

ቅርፊታቸውን ልጦ፣

ወዲያ ጣላቸው።

8የልጅነት ዕጮኛዋን1፥8 ወይም የልጅነት ባሏ እንዳጣች ድንግል1፥8 ወይም ወጣት ሴት

ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ።

9የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን፣

ከእግዚአብሔር ቤት ተቋርጧል፤

በእግዚአብሔርም ፊት የሚያገለግሉ፣

ካህናት ያለቅሳሉ።

10ዕርሻዎች ባዷቸውን ቀርተዋል፤

ምድሩም ደርቋል1፥10 ወይም መሬቱ ያዝናል

እህሉ ጠፍቷል፤

አዲሱ የወይን ጠጅ ዐልቋል፤

ዘይቱም ተሟጧል።

11እናንት ገበሬዎች፣ ዕዘኑ፤

እናንት የወይን ገበሬዎች፣ ዋይ በሉ፤

ስለ ገብሱና ስለ ስንዴው አልቅሱ፤

የዕርሻው መከር ጠፍቷልና።

12ወይኑ ደርቋል፤

የበለስ ዛፉም ጠውልጓል፤

ሮማኑ፣ ተምሩና እንኮዩ፣

የዕርሻው ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤

ስለዚህ ደስታ፣

ከሰው ልጆች ርቋል።

የንስሓ ጥሪ

13ካህናት ሆይ፤ ማቅ ለብሳችሁ አልቅሱ፤

እናንተ በመሠዊያው ፊት የምታገለግሉ፣ ዋይ በሉ፤

እናንት በአምላኬ ፊት የምታገለግሉ፣

ኑ፤ ማቅ ለብሳችሁ ዕደሩ፤

የእህል ቍርባኑና የመጠጥ ቍርባኑ፣

ከአምላካችሁ ቤት ተቋርጧልና።

14ቅዱስ ጾምን ዐውጁ፤

የተቀደሰንም ጉባኤ ጥሩ፤

ሽማግሌዎችን ሰብስቡ፤

በምድሪቱ የሚኖሩትን ሁሉ፣

ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ጥሩ፤

ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ።

15ወዮ ለዚያ ቀን፤

የእግዚአብሔር ቀን ቀርቧልና፤

ሁሉን ከሚችል1፥15 ዕብራይስጡ ሻደይ ይለዋል። አምላክ እንደ ጥፋት ይመጣል።

16የሚበላ ምግብ፣

ከዐይናችን ፊት፣

ደስታና ተድላ፣

ከአምላካችን ቤት አልተቋረጠብንምን?

17ዘሩ በዐፈር ውስጥ1፥17 ለዚህ የገባው የዕብራይስጡ ቃል ትርጕም አይታወቅም።

በስብሶ ቀርቷል፤

ግምጃ ቤቶቹ ፈራርሰዋል፤

ጐተራዎቹም ተሰባብረዋል፤

እህሉ ደርቋልና።

18መንጎች እንደ ምን ጮኹ፣

ከብቶቹ ተደናግጠዋል፤

መሰማሪያ የላቸውምና፤

የበግ መንጎች እንኳ ተቸግረዋል።

19አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወደ አንተ እጣራለሁ፤

ያልተነካውን መሰማሪያ እሳት በልቶታልና፤

የዱሩን ዛፍ ሁሉ ነበልባል አቃጥሎታል።

20የዱር አራዊት እንኳ ወደ አንተ አለኸለኹ፤

ወራጁ ውሃ ደርቋል፤

ያልተነካውንም መሰማሪያ እሳት በልቶታል።