ኢሳይያስ 54 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 54:1-17

የወደፊቱ የጽዮን ክብር

1“አንቺ መካን፣

አንቺ ልጅ ወልደሽ የማታውቂ፣

ዘምሪ፤ እልል በዪ፤ በደስታ ጩኺ፤

አንቺ አምጠሽ የማታውቂ፣

ባል ካላት ሴት ይልቅ፣

የፈቷ ልጆች ይበዛሉና”

ይላል እግዚአብሔር

2“የድንኳንሽን ቦታ አስፊ፤

የድንኳንሽን መጋረጃዎች በትልቁ ዘርጊ፤

ፈጽሞ አትቈጥቢ፤

ገመዶችሽን አርዝሚአቸው፤

ካስማዎችሽንም ቀብቅቢ።

3ወደ ቀኝም ወደ ግራም ትስፋፊያለሽ፤

ዘሮችሽ መንግሥታትን ይወርሳሉ፤

በባድማ ከተሞቻቸውም ይኖራሉና።

4“አይዞሽ አትፍሪ፤ ኀፍረት አይገጥምሽም፤

ውርደት ስለማይደርስብሽ አትሸማቀቂ፤

የወጣትነት ኀፍረትሽን ትረሺዋለሽ፤

የመበለትነት ስድብሽንም ከእንግዲህ አታስታውሺውም።

5ባልሽ ፈጣሪሽ ነውና፤

ስሙም የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፤

ታዳጊሽ የእስራኤል ቅዱስ ነው፤

እርሱም የምድር ሁሉ አምላክ ይባላል።

6እንደ ተናቀች የልጅነት ሚስት፣

ከልብ እንዳዘነችና እንደ ተጠላች ሚስት፣

እግዚአብሔር እንደ ገና ይጠራሻል”

ይላል አምላክሽ

7“ለጥቂት ጊዜ ተውሁሽ፤

ነገር ግን በታላቅ ርኅራኄ መልሼ እሰበስብሻለሁ።

8ለጥቂት ጊዜ እጅግ ስለ ተቈጣሁ፣

ፊቴን ከአንቺ ሰወርሁ፤

ነገር ግን በዘላለማዊ ቸርነቴ፣

እራራልሻለሁ”

ይላል ታዳጊሽ እግዚአብሔር

9“ይህ ለእኔ የኖኅ ውሃ ምድርን ዳግመኛ እንዳያጥለቀልቃት እንደማልሁበት፣

እንደ ኖኅ ዘመን ነው፤

አሁንም አንቺን ዳግም እንዳልቈጣ፣

እንዳልገሥጽሽም ምያለሁ።

10ተራሮች ቢናወጡ፣

ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣

ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤

የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም”

ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር

11“አንቺ የተጨነቅሽ ከተማ ሆይ፤ በዐውሎ ነፋስ የተናወጥሽ፣ ያልተጽናናሽም፤

እነሆ፤ በከበሩ ድንጋዮች54፥11 በዕራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም። አስጊጬ እገነባሻለሁ፤

በሰንፔር ድንጋይም እመሠርትሻለሁ።

12ጕልላትሽን በቀይ ዕንቍ፣

በሮችሽን በሚያብረቀርቁ ዕንቍዎች፣

ቅጥሮችሽንም በከበሩ ድንጋዮች እሠራለሁ።

13ወንዶች ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤

የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል።

14በጽድቅ ትመሠረቻለሽ፤

የግፍ አገዛዝ ከአንቺ ይርቃል፤

የሚያስፈራሽ አይኖርም፤

ሽብር ከአንቺ ይርቃል፤

አጠገብሽም አይደርስም።

15ማንም ጕዳት ቢያደርስብሽ፣ ከእኔ አይደለም፤

ጕዳት ያደረሰብሽ ሁሉ ለአንቺ እጁን ይሰጣል።

16“እነሆ፤ የከሰሉ ፍም እንዲቀጣጠል የሚያራግበውን፣

የጦር መሣሪያ የሚያበጀውን፣ አንጥረኛውን የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤

ጥፋት እንዲያደርስም የፈጠርሁ እኔ ነኝ

አጥፊውንም የፈጠርሁ እኔ ነኝ፤

17በአንቺ ላይ እንዲደገን የተበጀ መሣሪያ ይከሽፋል፤

የሚከስሽንም አንደበት ሁሉ ትረቺያለሽ፤

እንግዲህ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፤

ከእኔ የሚያገኙትም ጽድቃቸው ይኸው ነው፤”

ይላል እግዚአብሔር