ኢሳይያስ 5 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 5:1-30

ስለ ወይን ቦታ የተነገረ ቅኔ

1ስለ ወዳጄ፣

ደግሞም ስለ ወይን ቦታው ልዘምር፤

ወዳጄ በለምለም ኰረብታ ላይ

የወይን ቦታ ነበረው።

2መሬቱን ቈፈረ፤ ድንጋይንም ለቅሞ አወጣ፤

ምርጥ የሆነውንም ወይን ተከለበት።

በመካከሉ መጠበቂያ ማማ ሠራ፤

የወይን መጭመቂያ ጕድጓድም አበጀ፤

ከዚያ መልካም ፍሬ ያፈራል ብሎ ዐሰበ፤

ነገር ግን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ።

3“እናንት በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፤

በእኔና በወይኔ ቦታ መካከል እስቲ ፍረዱ።

4ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን

ሊደረግለት ይገባ ነበር?

መልካም የወይን ፍሬ ያፈራል ብዬ

ስጠብቅ ለምን ኮምጣጣ ፍሬ አፈራ?

5እንግዲህ በወይኔ ቦታ

ምን እንደማደርግ ልንገራችሁ፤

ዐጥሩን እነቅላለሁ፤

ለጥፋት ይጋለጣል፤

ግንቡንም አፈርሳለሁ፣

መረጋገጫም ይሆናል።

6የማይኰተኰትና የማይታረም

ጠፍ መሬት አደርገዋለሁ፤

ኵርንችትና እሾኽም ይበቅልበታል፤

ዝናብም እንዳይዘንብበት

ደመናዎችን አዝዛለሁ።”

7የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር

የወይን ቦታው የእስራኤል ቤት ነው፤

የይሁዳ ሰዎችም

የደስታው አትክልት ናቸው።

ፍትሕን ፈለገ፤ ነገር ግን ደም ማፍሰስን አየ፤

ጽድቅን ፈለገ፤ ነገር ግን የጭንቅን ጩኸት ሰማ።

ወዮታና ፍርድ

8ስፍራ ለሌሎች እስከማይተርፍ፣

ቤትን በቤት ላይ በመጨመር፣

መሬትን ከመሬት ጋር በማያያዝ፣

ለብቻችሁ በምድር ተስፋፍታችሁ ለምትኖሩ ወዮላችሁ

9የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬ እየሰማ እንዲህ ሲል ተናገረ፤

“ታላላቅ ቤቶች ወና ይቀራሉ፣

የሚያማምሩም ቤቶች ኗሪ ያጣሉ።

10ከሩብ ጋሻ5፥10 በዕብራይስጥ፣ ሩብ ጋሻ መሬት በዐሥር ጥማድ በሬ በአንድ ቀን የሚታረስ ነው። የወይን ቦታ አንድ የባዶስ መስፈሪያ ያህል የወይን ጭማቂ ብቻ ይገኛል፤ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር ተዘርቶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ብቻ ይሰጣል።”5፥10 ምናልባት አንድ ባዶስ ሀያ ሁለት ሊትር ያህል ነው። አንድ የቆሮስ መስፈሪያ መቶ ስድሳ ኪሎ ግራም ያህል ነው። አንድ የኢፍ መስፈሪያ ዐሥራ ስምንት ኪሎ ግራም ያህል ነው።

11የሚያሰክር መጠጥ ፍለጋ

ማልደው ለሚነሡ፣

እስኪያነድዳቸውም ወይን በመጠጣት

ሌሊቱን ለሚያነጉ ወዮላቸው!

12በግብዣቸው ላይ በገናና መሰንቆ፣

ከበሮና ዋሽንት እንዲሁም የወይን ጠጅ አለ፤

ነገር ግን ለእግዚአብሔር ሥራ ቦታ አልሰጡም፤

ለእጆቹም ሥራ ክብር አላሳዩም።

13ስለዚህ ሕዝቤ

ዕውቀት በማጣቱ ይማረካል፤

መኳንንቱም በራብ ይሞታሉ፤

ሕዝቡም በውሃ ጥም ይቃጠላል።

14ስለዚህ ሲኦል5፥14 በዕብራይስጡ፣ መቃብር ማለት ነው። ሆዷን አሰፋች፣

አፏንም ያለ ልክ ከፈተች፤

መኳንንቱና ሕዝቡ ከረብሸኞቻቸውና ከጨፋሪዎቻቸው ጋር

ወደዚያ ይወርዳሉ።

15ሰው ይዋረዳል፤

የሰው ልጅም ዝቅ ዝቅ ይላል፤

የእብሪተኛውም ዐይን ይሰበራል።

16የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን በፍትሕ ከፍ ከፍ ይላል፤

ቅዱሱም አምላክ ቅድስናውን በጽድቅ ይገልጻል።

17በጎችም በገዛ መሰማሪያቸው እንደሚሰማሩ ሆነው ይግጣሉ፤

የበግ ጠቦቶችም በባለጠጎች ፍርስራሽ ላይ ሣር ይበላሉ5፥17 በዕብራይስጡ፣ እንግዶች ይበሉታል ይለዋል።

18ኀጢአትን በማታለል ገመድ ለሚስቡ፣

በደልንም በሠረገላ ማሰሪያ ለሚጐትቱ ወዮላቸው!

19“በዐይናችን እንድናይ

እግዚአብሔር ይቸኵል፤

ሥራውንም ያፋጥን፤

የእስራኤልን ቅዱስ፣ የእርሱን ዕቅድ

እንድናውቃት ትቅረብ፤

ትምጣም” ለሚሉ ወዮላቸው!

20ክፉውን መልካም፣

መልካሙን ክፉ ለሚሉ

ብርሃኑን ጨለማ፣

ጨለማውን ብርሃን ለሚያደርጉ፣

ጣፋጩን መራራ፣

መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!

21ራሳቸውን እንደ ብልኅ ለሚቈጥሩ፣

በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው!

22የወይን ጠጅ ለመጠጣት ጀግኖች፣

የሚያሰክር መጠጥ ለመደባለቅ ብርቱ ለሆኑ ወዮላቸው!

23ጕቦን በመቀበል በደለኛን ንጹሕ ለሚያደርጉ፣

ለበደል አልባ ሰው ፍትሕን ለሚነፍጉ ወዮላቸው!

24ስለዚህ የእሳት ነበልባል ገለባን እንደሚበላ፣

ድርቆሽም በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ፣

የእነርሱም ሥር እንዲሁ ይበሰብሳል፤

አበባቸውም እንደ ትቢያ ይበንናል፤

የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ሕግ ንቀዋልና፤

የእስራኤል ቅዱስ የተናገረውንም ቃል አቃልለዋል።

25የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነድዷል፤

እጁን አንሥቶ መትቷቸዋል፤

ተራሮች ራዱ፤

ሬሳዎችም በመንገድ ላይ እንደ ተጣለ ጥራጊ ሆኑ፤

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቍጣው ገና አልተመለሰም፤

እጁም እንደ ተነሣ ነው።

26ከሩቅ ያሉትን ሕዝቦች የሚጠራበትን

ምልክት ያቆማል፤

ከምድር ዳርቻም በፉጨት ይጠራቸዋል፤

እነርሱም እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ።

27በመካከላቸው ደካማና ስንኩል አይገኝም፤

የሚያንቀላፋና የሚተኛ አይኖርም፤

የወገባቸው መቀነት አይላላም፤

የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም።

28ፍላጻቸው የተሳለ፣

ቀስታቸውም የተደገነ ነው፤

የሠረገሎቻቸውም መንኰራኵሮች እንደ

ዐውሎ ነፋስ ናቸው።

29ጩኸታቸው እንደ አንበሳ ነው፤

እንደ አንበሳ ደቦል ያገሣሉ፤

ያደኑትንም ይዘው ይጮኻሉ፤

ተሸክመውት ይሄዳሉ፤ የሚያስጥልም የለም።

30በዚያን ቀን

እንደ ባሕር ሞገድ ይጮኹበታል፤

ማንም ወደ ምድር ቢመለከት፣

ጨለማንና መከራን ያያል፤

ብርሃን እንኳ በደመናዎች ይጋረዳል።