ኢሳይያስ 43 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 43:1-28

የእስራኤል ብቸኛ አዳኝ

1አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ! የፈጠረህ፣

እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤

በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤

2በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣

ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤

ወንዙን ስትሻገረው፣

አያሰጥምህም፤

በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣

አያቃጥልህም፤

ነበልባሉም አይፈጅህም።

3እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣

የእስራኤልም ቅዱስ መድኀኒትህ ነኝና፤

ግብፅን ለአንተ ቤዛ እንድትሆን፣

ኢትዮጵያንና ሳባን በአንተ ፈንታ እሰጣለሁ።

4ለዐይኔ ብርቅና ክቡርም ስለ ሆንህ፣

እኔም ስለምወድድህ፣

ሰዎችን በአንተ ምትክ፣

ሕዝቦችንም በሕይወትህ ፈንታ እሰጣለሁ።

5ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤

ልጆችህን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤

ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።

6ሰሜንን፣ ‘አምጣ’፣

ደቡብንም፣ ‘ልቀቅ’ እላለሁ፤

ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣

ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣

7በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣

ለክብሬ የፈጠርሁትን፣

ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።”

8ዐይን እያላቸው የታወሩትን፣

ጆሮ እያላቸው የደነቈሩትን አውጣ።

9ሕዝብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰብ፤

ሰውም ይከማች፤

ከእነርሱ አስቀድሞ ይህን የነገረን፣

የቀድሞውን ነገር ያወጀልን ማን ነው?

ሌሎችን ሰምተው፣ “እውነት ነው” እንዲሉ፣

ትክክለኝነታቸውም እንዲረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያቅርቡ።

10“ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣

እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣

እናንተ ምስክሮቼ፣

የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር

“ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤

ከእኔም በኋላ አይኖርም።

11እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም።

12ገልጫለሁ፤ አድኛለሁ፤ ተናግሬአለሁ፤

በመካከላችሁ እኔ እንጂ ባዕድ አምላክ አልነበረም።

እኔ አምላክ እንደ ሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር

13“ከጥንት ጀምሮ እኔው ነኝ፤

ከእጄም ማውጣት የሚችል የለም፤

እኔ የምሠራውን ማን ማገድ ይችላል?”

የእግዚአብሔር ምሕረትና የእስራኤል አለመታመን

14የእስራኤል ቅዱስ፣

የሚቤዣችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ስለ እናንተ በባቢሎን43፥14 ወይም፣ ከለዳውያን ማለት ነው። ላይ ሰራዊት እሰድዳለሁ፤

በሚመኩባቸውም መርከቦች፣

ባቢሎናውያንን ሁሉ እንደ ኰብላይ አመጣለሁ።

15እኔ እግዚአብሔር፣ የእናንተ ቅዱስ፣

የእስራኤል ፈጣሪ፣ ንጉሣችሁ ነኝ።”

16በባሕር ውስጥ መንገድ፣

በማዕበል ውስጥ መተላለፊያ ያበጀ፣

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

17እንደ ገና ላይነሡ እዚያው እንዲተኙ፣

እንደ ጧፍ ኵስታሪ ረግፈው እንዲጠፉ፣

ሠረገሎችንና ፈረሶችን፣

ሰራዊቱንና ደጀኑን በአንድነት ያወጣ እንዲህ ይላል፤

18“የቀደመውን ነገር አታስቡ፤

ያለፈውን እርሱ።

19እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ፤

እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን?

በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤

በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤

20የምድረ በዳ አራዊት፣

ቀበሮና ጕጕት ያከብሩኛል፤

በምድረ በዳ ውሃ፣

በበረሓም ምንጭ እሰጣለሁና።

ለመረጥሁት ሕዝቤ ውሃ እሰጣለሁ፤

21ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ

ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ይህን አደርጋለሁ።

22“ያዕቆብ ሆይ፤ አንተ ግን አልጠራኸኝም፤

እስራኤል ሆይ፤ የእኔ ነገር ታክቶሃል።

23ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎች አላመጣህልኝም፤

በመሥዋዕትህም አላከበርኸኝም።

በእህል ቍርባን አላስቸገርሁህም፤

በዕጣን መሥዋዕትም አላሰለቸሁህም።

24መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን አልገዛህልኝም፤

በመሥዋዕትህ ሥብ አላጠገብኸኝም፤

ነገር ግን የኀጢአት ሸክምህን ጫንህብኝ፤

በበደልህም አደከምኸኝ።

25“ስለ ራሴ ስል መተላለፍህን የምደመስስልህ፣

እኔ፣ እኔው ነኝ፤

ኀጢአትህን አላስባትም።

26እስቲ ያለፈውን አስታውሰኝ፤

ተቀራርበን እንከራከርበት፤

ትክክለኛ ስለ መሆንህም አስረዳ።

27የመጀመሪያው አባትህ ኀጢአት ሠርቷል፤

መምህሮችህም ዐምፀውብኛል።

28ስለዚህ የመቅደስህን አለቆች አዋርዳለሁ፤

ያዕቆብን ለጥፋት፣43፥28 የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠትን ያመለክታል።

እስራኤልን ለስድብ እዳርጋለሁ።