ኢሳይያስ 37 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 37:1-38

የኢየሩሳሌም ዐርነት ታወጀ

1ንጉሡ ሕዝቅያስ ይህን ሲሰማ፣ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለበሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ገባ። 2የቤተ መንግሥቱን አስተዳዳሪ ኤልያቄምንና ጸሓፊውን ሳምናስን እንዲሁም ከካህናቱ ዋና ዋናዎቹን ማቅ ለብሰው ሁሉም ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲሄዱ ላካቸው። 3እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፤ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የተግሣጽና የውርደት ቀን ነው፤ ሕፃናት ሊወለዱ ሲሉ ብርታት እንደሚታጣበት ቀን ሆኗል። 4ሕያው አምላክን ይገዳደር ዘንድ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የጦር አዛዡን ቃል እግዚአብሔር አምላክህ ይሰማ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አምላክህም ሰምቶ ይገሥጸው ይሆናል፤ ስለዚህ አንተም በሕይወት ለተረፉት ቅሬታዎች ጸልይ።’ ”

5የንጉሡ የሕዝቅያስ መልእክተኞች ወደ ኢሳይያስ መጡ፤ 6ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፤ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአሦር ንጉሥ ባሪያዎች እኔን ስለ ሰደቡኝ፣ በሰማኸው ቃል አትሸበር። 7እነሆ፤ በላዩ መንፈስን እሰድዳለሁ፤ ወሬም ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።’ ”

8የጦር አዛዡም፣ የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ለቅቆ መሄዱን ሲሰማ፣ ከነበረበት ተመለሰ፤ ንጉሡም የልብናን ከተማ ሲወጋ አገኘው።

9ደግሞም ሰናክሬም፣ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቲርሐቅ ሊወጋው መምጣቱን ሰማ፤ ይህንም እንደ ሰማ ወደ ሕዝቅያስ መልእክተኞች ላከ፤ እንዲህም አለ፤ 10“ለይሁዳ ንጉሥ ለሕዝቅያስ እንዲህ በሉት፤ ‘ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ አትያዝም’ ብሎ የተማመንህበት አምላክ አያታልልህ። 11እነሆ፤ የአሦር ነገሥታት በአገሮች ሁሉ ላይ ያደረጉትን፣ ፈጽሞም እንዳጠፏቸው ሰምተሃል፤ አንተስ የምታመልጥ ይመስልሃልን? 12የቀደሙት አባቶቼ ያጠፏቸውን፣ የጎዛንን፣ የካራንን፣ የራፊስን እንዲሁም በተላሳር የሚኖሩ የዔድንን ሰዎች የአሕዛብ አማልክት አድነዋቸዋልን? 13የሐማት ንጉሥ፣ የአርፋድ ንጉሥ፣ የሴፈርዋይም ከተማ ንጉሥ፣ የሄና ንጉሥ ወይም የዒዋ ንጉሥ የት አሉ?”

የሕዝቅያስ ጸሎት

14ሕዝቅያስ ደብዳቤውን ከመልእክተኞቹ ተቀብሎ አነበበው፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጥቶም ደብዳቤውን በእግዚአብሔር ፊት ዘረጋው። 15ሕዝቅያስም እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 16“በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በምድር ባሉ መንግሥታት ሁሉ ላይ አንተ ብቻ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርንም ፈጥረሃል። 17አቤቱ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጆሮህን አዘንብል፤ አድምጥም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐይኖችህን ክፈት፤ ተመልከትም። ሰናክሬም ሕያው አምላክን ለመሳደብ የላከውን ቃል ስማ።

18እግዚአብሔር ሆይ፤ በርግጥ የአሦር ነገሥታት እነዚህን ሕዝቦች፣ ምድራቸውንም ሁሉ ባድማ አድርገዋል። 19አማልክታቸውን ወደ እሳት ጥለዋል፤ በሰው እጅ የተቀረጹ የድንጋይና የዕንጨት ምስሎች እንጂ አማልክት አልነበሩምና። 20አሁንም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ እግዚአብሔር ብቻ አምላክ እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ፣ አቤቱ ከእጁ አድነን።”

የሰናክሬም ውድቀት

21ከዚህ በኋላ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ስለ አሦር ንጉሥ፣ ስለ ሰናክሬም ወደ እኔ ጸልየሃልና፣ 22እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤

“ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ፣

ንቃሃለች፣ አፊዛብሃለች፤

የኢየሩሳሌም ልጅ፣

አንተ ስትሸሽ ራሷን ነቅንቃብሃለች።

23የሰደብኸውና ያቃለልኸው ማንን ነው?

ድምፅህንስ ከፍ ከፍ ያደረግኸው፣

ዐይንህን በትዕቢት ያነሣኸው በማን ላይ ነው?

በእስራኤል ቅዱስ ላይ ነው እኮ!

24በመልእክተኞችህ በኩል፣

በጌታ ላይ ብዙ የስድብ ቃል ተናገርህ፤

እንዲህም አልህ፤

‘በሠረገሎቼ ብዛት፣

የተራሮችንም ከፍታ፣

የሊባኖስንም ጫፍ ወጥቻለሁ፤

ረጃጅም ዝግባዎችን፣

የተመረጡ ጥዶችን ቈርጫለሁ፤

እጅግ ወደራቁት ከፍታዎች፣

እጅግ ውብ ወደሆኑትም ደኖች ደርሻለሁ፤

25በባዕድ ምድር37፥25 የሙት ባሕር ቅጆች (እንዲሁም 2ነገ 19፥24 ይመ) ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ በባዕድ ምድር የሚለውን ሐረግ አይጨምርም። ጕድጓዶችን ቈፈርሁ፤

ከዚያም ውሃ ጠጣሁ።

የግብፅን ምንጮች ሁሉ፣

በእግሬ ረግጬ አደረቅሁ።’

26“ይህን ቀድሞ እንደ ወሰንሁት፣

ጥንትም እንዳቀድሁት፣

አልሰማህምን?

አሁን ደግሞ እንዲፈጸም አደረግሁት፤

አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የድንጋይ

ክምር አደረግሃቸው።

27የሕዝቦቻቸው ኀይል ተሟጥጧል፤

ደንግጠዋል፤ ተዋርደዋልም፤

በሜዳ እንዳሉ ዕፀዋት፣

እንደ ለጋ ቡቃያ፣

በሰገነት ላይ እንደ በቀለ ሣር፣

በእንጭጩ ዋግ እንደ መታው ሆነዋል።

28“ ‘እኔ ግን የት እንዳለህ፣

መምጣት መሄድህ ምን ጊዜ እንደ ሆነ፣

በእኔም ላይ እንዴት በቍጣ እንደምትነሣሣ ዐውቃለሁ።

29በእኔ ላይ በቍጣ ስለ ተነሣሣህ፣

እብሪትህም ወደ ጆሮዬ ስለ ደረሰ፣

በአፍንጫህ ስናጌን፣

በአፍህ ልጓሜን አገባለሁ፤

በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስ

አደርግሃለሁ።’

30“ሕዝቅያስ ሆይ፤ ይህ ምልክት ይሆንልሃል፤

“በዚህ ዓመት የገቦውን፣

በሚቀጥለው ዓመት ከገቦው የበቀለውን ትበላላችሁ፤

በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤

ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።

31እንደ ገናም የይሁዳ ቤት ቅሬታ፣

ሥሩን ወደ ታች ይሰድዳል፤ ከላይም ፍሬ ያፈራል፤

32ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣

የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና፤

የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅናት

ይህን ያደርጋል።

33“ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤

“ወደዚች ከተማ አይገባም፤

ፍላጻ አይወረውርባትም፤

ጋሻ አንግቦ አይመጣባትም፤

በዐፈር ቍልልም አይከብባትም።

34በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤

ወደዚች ከተማም አይገባም”

ይላል እግዚአብሔር

35“ስለ ራሴና፣ ስለ አገልጋዬም ስለ ዳዊት፣

ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።”

36ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ ሰው ገደለ፤ በሰፈር ያሉት ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር። 37ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም አመለጠ፤ ወደ ነነዌም ተመልሶ በዚያ ተቀመጠ።

38ሰናክሬም በአምላኩ በናሳራክ ቤተ ጣዖት በሚሰግድበት ጊዜ፣ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገደሉት፤ ከዚያም ወደ አራራት ምድር ኰበለሉ፤ ልጁም አስራዶን በምትኩ ነገሠ።