ኢሳይያስ 33 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 33:1-24

የጭንቅ ጊዜና ርዳታ

1አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፣

አንት አጥፊ፣ ወዮልህ!

አንተ ሳትካድ የምትክድ፣

አንት ከዳተኛ፣ ወዮልህ!

ማጥፋትን በተውህ ጊዜ፣

ትጠፋለህ፤

ክሕደትህንም በተውህ ጊዜ ትከዳለህ።

2እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረን፤

አንተን ተስፋ አድርገናል።

በየማለዳው ብርታት፣

በጭንቅ ጊዜም ድነት ሁነን።

3ሕዝቦች በድምፅህ ነጐድጓድ ይሸሻሉ፤

መንግሥታት ስትነሣ ይበተናሉ።

4ሕዝቦች ሆይ፤ አንበጣ እንደሚሰበስብ ብዝበዛችሁም ይሰበሰባል፤

ሰዎችም እንደ ኵብኵባ ይጨፍሩበታል።

5እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጧልና ከፍ ከፍ አለ፤

ጽዮንን በጽድቅና በፍትሕ ይሞላታል።

6እርሱ ለዘመንህ የሚያስተማምን መሠረት፣

የድነት፣ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ ይሆናል፤

እግዚአብሔርንም መፍራት የዚህ ሀብት ቍልፍ ነው33፥6 ወይም እግዚአብሔርን መፍራት ከእግዚአብሔር የሆነ ሀብት ነው

7እነሆ፤ ጐበዞቻቸው በየመንገዱ ይጮኻሉ፤

የሰላም መልእክተኞችም አምርረው ያለቅሳሉ።

8አውራ ጐዳናዎች ባዶ ናቸው፤

በመንገድ ላይ ሰው የለም፤

ስምምነቱ ፈርሷል፤

መካሪዎቹ33፥8 የሙት ባሕር ጥቅልሎች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን፣ ከተሞች ይላል። ተንቀዋል፤

የሚከበርም የለም።

9ምድሪቱ አለቀሰች33፥9 ወይም ደረቀች (ጠወለገች)፤ መነመነች፤

ሊባኖስ ዐፈረች፤ ጠወለገች፤

ሳሮን እንደ ዓረባ ምድረ በዳ ሆነች፤

ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ።

10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አሁን እነሣለሁ፤

አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ፤

አሁን እከብራለሁ።

11ገለባን ፀነሳችሁ፤

እብቅንም ወለዳችሁ፤

እስትንፋሳችሁም የሚበላችሁ እሳት ነው።

12ሕዝቦች ኖራ እንደሚወጣው ድንጋይ ይቃጠላሉ፤

እንደ እሾኽ ቍጥቋጦ በእሳት ይጋያሉ።”

13እናንት በሩቅ ያላችሁ ያደረግሁትን ስሙ፤

እናንት በቅርብ ያላችሁ ኀይሌን ዕወቁ!

14በጽዮን ያሉ ኀጢአተኞች ደነገጡ፤

አምላክ የሌላቸውም ፍርሀት ይዟቸው፣

“ከእኛ መካከል ከሚባላ እሳት ጋር ማን መኖር ይችላል፣

ከዘላለም እሳትስ ጋር ማን መኖር ይችላል?” አሉ።

15በጽድቅ የሚራመድ፣

ቅን ነገር የሚናገር፣

በሽንገላ የሚገኝን ትርፍ የሚንቅ፣

መማለጃን ላለመቀበል እጁን የሚሰበስብ፣

የግድያን ሤራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣

ክፋትን ላለማየት ዐይኑን የሚጨፍን፣

16ይህ ሰው በከፍታ ላይ ይኖራል፤

የተራራም ምሽግ መጠጊያው ይሆናል፤

እንጀራ ይሰጠዋል፣

ውሃውም አይቋረጥበትም።

17ዐይኖችህ ንጉሡን በውበቱ ያዩታል፤

በሩቅ የተዘረጋችውንም ምድር ይመለከታሉ።

18የቀደመው መከራ ትዝ እያለህ፣

“ያ ዋና አለቃ የት አለ?

ግብር ተቀባዩስ ወዴት ሄደ?

የመጠበቂያ ማማ ኀላፊውስ የት አለ?” ትላለህ።

19እነዚያ ንግግራቸው የማይገባ፣

የሚሉትም የማይታወቅ፣

ሊረዱት የማይቻል ቋንቋ የሚናገሩትን ጋጠወጥ ሕዝብ ከእንግዲህ አታያቸውም።

20በዓላታችንን የምናከብርባትን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤

ሰላማዊ መኖሪያ፣ የማትነቃነቅ ድንኳን የሆነችውን፣

ካስማዋ የማይነቀል፣

ከገመዷ አንዱ እንኳ የማይበጠሰውን፣

ኢየሩሳሌምን ዐይኖችህ ያያሉ።

21እግዚአብሔር በዚያ ኀይላችን ይሆናል፤

ባለ መቅዘፊያ ጀልባዎች እንደማያልፉባቸው፣

ታላላቅ መርከቦችም እንደማይሻገሯቸው፣

ሰፋፊ ወንዞችና ጅረቶች ይሆንልናል።

22እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤

እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤

እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤

የሚያድነንም እርሱ ነውና።

23መወጠሪያ ገመድህ ላልቷል፤

ምሰሶው ጠብቆ አልተተከለም፤

ሸራው አልተወጠረም፤

በዚያ ጊዜ ታላቅ ምርኮ ይከፋፈላል፤

ዐንካሳ እንኳ ሳይቀር ምርኮ ይወስዳል።

24በጽዮን ተቀምጦ፣ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም፤

በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአትም ይቅር ይባላል።