ኢሳይያስ 3 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 3:1-26

በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የሚመጣ ፍርድ

1እነሆ፤ ጌታ፣

የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ

ድጋፉንና ርዳታውን፣

የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤

2ጀግናውንና ተዋጊውን፣

ፈራጁንና ነቢዩን፣

አስማተኛውንና ሽማግሌውን፣

3የአምሳ አለቃውንና ባለ ማዕረጉን፣

አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለሙያ፣

ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል።

4ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤

ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል።

5ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤

ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፣

ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፣

ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል።

6ሰውም በአባቱ ቤት

ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፣

“አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤

ይህንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ!” ይለዋል።

7እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣

“እኔ መፍትሔ አልሆንም፤

በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤

የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል።

8ኢየሩሳሌም ተንገዳግዳለች፤

ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤

ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚቃወም፣

የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና።

9የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤

ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤

አይደብቁትምም፤

ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ፣

ወዮላቸው!

10ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤

የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና።

11በደለኞች ወዮላቸው፤ ጥፋት ይመጣባቸዋል፤

የእጃቸውን ያገኛሉና።

12ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤

ሴቶችም ይገዟቸዋል።

ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤

ከመንገድህም መልሰውሃል።

13እግዚአብሔር በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጧል፤

በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቷል።

14እግዚአብሔር

ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋር እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤

“የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤

ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤

15ሕዝቤን በችግር ስታደቅቁት፣

የድኾችንም ፊት በሐዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?”

ይላል ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

16እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤

ዐንገታቸውን እያሰገጉ፣

በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤

እየተቈነኑ በመራመድ፣

የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ።

17ስለዚህ፣ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይ

ቈረቈር ያመጣል፤

እግዚአብሔርም ራሳቸውን ቡሀ ያደርጋል።

18በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፣ የጠጕር ጌጡን፣ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፣ 19የጆሮ ጕትቻውን፣ የእጅ አንባሩን፣ የፊት መሸፈኛውን፣ 20የራስ መሸፈኛውን፣ ዐልቦውን፣ ሻሹን፣ የሽቶ ብልቃጡን፣ አሸንክታቡን፣ 21የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፣ 22ያማረውን ቀሚስ፣ የውስጥ ልብሱን፣ ካባውን፣ የእጅ ቦርሳውን፣ 23መስተዋቱን፣ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፣ የራስ ጌጡን፣ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል።

24በሽቶ ፈንታ ግማት፣

በሻሽ ፈንታ ገመድ፣

አምሮ በተሠራ ጠጕር ፈንታ ቡሀነት፣

ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፣

በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል።

25ወንዶቻችሁ በሰይፍ ስለት፣

ተዋጊዎቻችሁ በጦርነት ይወድቃሉ።

26የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤

እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች።