ኢሳይያስ 29 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 29:1-24

ወዮ ለዳዊት ከተማ

1ዳዊት የሰፈረብሽ ከተማ፣

አርኤል፣ አርኤል ወዮልሽ!

ዓመት በዓመት ላይ ጨምሪ፣

ዐውደ ዓመትሽም ይቀጥል።

2ነገር ግን አርኤልን29፥2 በዕብራይስጡ፣ የመሠዊያ መሬት የሚለው ቃል ድምፀት፣ አርኤል ከሚለው ቃል ጋር አንድ ዐይነት ነው። እከብባለሁ፤

ታለቅሳለች፤ ዋይ ዋይ ትላለች፤

ለእኔም እንደ መሠዊያ ስፍራ ትሆንልኛለች።

3በዙሪያሽ እሰፍራለሁ፤

በቅጥር እከብብሻለሁ፤

የከበባ ዐምባም ሠርቼ አስጨንቅሻለሁ።

4ወደ ታች ትወርጃለሽ፤ ከምድርም በታች ትናገሪያለሽ፤

ንግግርሽ ከትቢያ እየተጕተመተመ ይወጣል፤

ድምፅሽ እንደ መናፍስት ድምፅ ከመሬት ወደ ላይ ይመጣል፤

ንግግርሽ ከትቢያ ያንሾካሹካል።

5ነገር ግን ብዙ ጠላቶችሽ እንደ ትቢያ ብናኝ፣

የጨካኞች መንጋ በነፋስ እንደሚነዳ

ገለባ ይሆናሉ።

ድንገት ሳይታሰብም፣

6የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር

በነጐድጓድ፣ በምድር መናወጥና በታላቅ ድምፅ፣

በዐውሎ ነፋስና በኀይለኛ ሞገድ፣ ፈጽሞ በሚባላም የእሳት ነበልባል ይመጣል።

7አርኤልን የሚወጋ የአሕዛብ ሁሉ መንጋ፣

በእርሷና በምሽጓ ላይ አደጋ የሚጥልና የሚከብባት፣

እንደ ሕልም

በሌሊትም እንደሚታይ ራእይ ይሆናል።

8የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ዐድሮ፣

ነገር ግን ሲነቃ ራቡ እንዳልለቀቀው፣

የጠማውም ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ዐድሮ፣

ነገር ግን ሲነቃ እንደ ዛለና ጥማቱም እንዳልተወው፣

የጽዮንን ተራራ የሚወጋ፣

የአሕዛብ መንጋ ሁሉ እንዲሁ ይሆናል።

9ነኹልሉ ተደነቁም፤

ተጨፈኑ፤ እስከ ወዲያኛውም ታውራችሁ ቅሩ፤

በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ስከሩ፤

በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳገዱ።

10እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ ጥሎባችኋል፤

ዐይኖቻችሁን፣ ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤

ራሶቻችሁን፣ ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።

11ይህ ሁሉ ራእይ በጥቅልል መጽሐፍ ውስጥ እንደ ታሸገ ቃል ሆኖባችኋል። ጥቅልሉንም መጽሐፍ ማንበብ ለሚችል ሰው፣ “እባክህ አንብብልን” ብላችሁ ብትሰጡት፣ “ታሽጓልና አልችልም” ይላችኋል። 12ደግሞም ጥቅልሉን መጽሐፍ ማንበብ ለማይችል ሰው፣ “እባክህን አንብብልን” ብላችሁ ብትሰጡ፣ “ማንበብ አልችልም” ይላችኋል።

13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባል፤

በከንፈሩም ያከብረኛል፤

ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤

የሚያመልከኝም፣

ሰው ባስተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው29፥13 ዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን፣ በከንቱ ያመልኩኛል፤ ትምህርታቸው ሰው ያሰተማረው ሰው ሠራሽ ሥርዐት ብቻ ነው ይላል።

14ስለዚህ ይህን ሕዝብ በድንቅ ላይ ድንቅ

ነገር እያደረግሁ፣

ዳግመኛ አስገርመዋለሁ፤

የጥበበኞች ጥበብ ይጠፋል፤

የአስተዋዮችም ማስተዋል ይበንናል።”

15ሐሳባቸውን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ፣

ወደ ጥልቅ ጕድጓድ ለሚወርዱ

ሥራቸውንም በጨለማ ለሚያከናውኑ፣

“ማን ያየናል? ማንስ ያውቅብናል” ለሚሉ ወዮላቸው!

16እናንተ ነገሮችን ትገለብጣላችሁ

ሸክላ ሠሪውን እንደ ሸክላ ትመለከታላችሁ፤

ለመሆኑ፣ ተሠሪ ሠሪውን፣

“እርሱ አልሠራኝም” ይለዋልን?

ሸክላ የሠራውን፣

“እርሱ ምንም አያውቅም” ይለዋልን?

17ሊባኖስ ወደ ለም ዕርሻነት ለመለወጥ፣

ለም የሆነውም መሬት ወደ ዱርነት ለመለወጥ ጥቂት ጊዜ አልቀረውምን?

18በዚያን ጊዜ ደንቈሮ የጥቅልሉን መጽሐፍ ቃል ይሰማል፤

የዐይነ ስውሩም ዐይኖች

ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ።

19ትሑታን በእግዚአብሔር

ምስኪኖችም በእስራኤል ቅዱስ እንደ ገና ሐሤት ያደርጋሉ።

20ጨካኞች እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤

ፌዘኞችም በንነው ይጠፋሉ፤

ለክፋት ያደፈጡ ሁሉ ይወገዳሉ።

21ሰውን በነገር በደለኛ የሚያደርጉ፣

በተከሳሽ ላይ ወጥመድ የሚዘረጉ፣

በሐሰት ምስክር ፍትሕን ከንጹሓን የሚቀሙ ይቈረጣሉ።

22ስለዚህ አብርሃምን የተቤዠው እግዚአብሔር

ለያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፤

“ያዕቆብ ከእንግዲህ ወዲያ አያፍርም፤

ፊቱም ከእንግዲህ አይለዋወጥም።

23በመካከላቸው የእጄ ሥራ የሆኑ፣

ልጆቻቸውን ሲያዩ፣

ስሜን ይቀድሳሉ፤

የያዕቆብን ቅዱስ ቅድስና ያውቃሉ፤

በእስራኤልም አምላክ ፊት በፍርሀት ይቆማሉ።

24በመንፈስ የሳቱ ያስተውላሉ፤

የሚያጕረመርሙም ምክር ይቀበላሉ።”