ኢሳይያስ 27 – New Amharic Standard Version NASV

New Amharic Standard Version

ኢሳይያስ 27:1-13

የእስራኤል ዐርነት መውጣት

1በዚያ ቀን እግዚአብሔር

ተወርዋሪውን እባብ ሌዋታንን፣

የሚጠቀለለውን ዘንዶ ሌዋታንን

በብርቱ፣ በታላቁና በኀይለኛ ሰይፍ ይቀጣዋል፤

የባሕሩንም ግዙፍ አውሬ ይቈራርጠዋል።

2በዚያን ቀን እንዲህ ይባላል፤

“ለመልካሙ የወይን ቦታ ዘምሩለት፤

3እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤

ዘወትር ውሃ አጠጣዋለሁ፤

ስለዚህ ማንም አይጐዳውም፣

ቀንና ሌሊት እጠብቀዋለሁ፤

4እኔ አልቈጣም።

እሾኽና ኵርንችት ምነው በተነሡብኝ!

ለውጊያ በወጣሁባቸው፣

አንድ ላይ ባቃጠልኋቸው!

5አለዚያ ይምጡና መሸሸጊያቸው ያድርጉኝ፤

ከእኔ ጋር ሰላም ይፍጠሩ፤

አዎን፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርጉ።”

6በሚመጡት ቀናት ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፤

እስራኤልም ያቈጠቍጣል፣ ያብባልም፤

በፍሬያቸውም ምድርን ሁሉ ይሞላሉ።

7የመቷትን እንደ መታቸው፣

እግዚአብሔር እርሷንስ መታትን?

የገደሏትን እንደ ገደላቸው፣

እርሷስ ተገደለችን?

8በጦርነትና በስደት ተፋለምሃት27፥8 በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጕም በትክክል አይታወቅም።

የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን፣

በብርቱ ዐውሎ ነፋስ አሳደድሃት።

9ያዕቆብ የመሠዊያ ድንጋዮችን፣

እንደ ኖራ ድንጋይ ፈጭቶ ሲያደቅቃቸው፣

የአሼራን ዐምድና የዕጣን መሠዊያዎችን፣

ከቦታቸው ነቅሎ ሲጥል፣

በዚያን ጊዜ በደሉ ይሰረይለታል፤

ይህም ኀጢአቱን የማስወገዱ ሙሉ ፍሬ ይሆናል።

10የተመሸገባት ከተማ ባዶዋን ቀርታለች፤

እንደ ምድረ በዳም የተተወች ስፍራ ሆናለች፤

ጥጆች በዚያ ይሰማራሉ፤

እዚያም ይተኛሉ፤

ቅርንጫፎቿንም ልጠው ይበላሉ።

11ጫፎቿ ሲደርቁ ይሰበራሉ፤

ሴቶችም መጥተው ይማግዷቸዋል።

ማስተዋል የሌለው ሕዝብ ስለሆነ፣

ፈጣሪው አይራራለትም፤

ያበጀውም አይምረውም።

12በዚያ ቀን ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ እስከ ግብፅ ደረቅ ወንዝ፣ እግዚአብሔር እህሉን ይወቃል፤ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፤ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ። 13በዚያ ቀን ታላቅ መለከት ይነፋል፤ በአሦር የጠፉትና በግብፅ የተሰደዱትም መጥተው፣ በተቀደሰው ተራራ በኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ያመልካሉ።